Search

የቀይ መለዮ ባለአደራዎቹ ተተኪ ኮማንዶዎች እና የጀግንነት ታሪክን የማስቀጠል ዝግጁነት

ሓሙስ ሰኔ 25, 2018 128

ኢትዮጵያ ወደፊት የሚያጋጥሟትን ማናቸውንም ተገማች ፈተናዎች በብቃት ሊያሻግሯት የሚችሉ ተተኪ ጀግኖችን በከፍተኛ ደረጃ እያፈራች መሆኑን የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ አስታወቁ።

ዋና አዛዡ ከማሰልጠኛ አመራሮች፣ ከአሰልጣኞች እና ከሰልጣኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ የሀገራችን ሰላም በዘላቂነት እንዲረጋገጥ ዕዙ በተሰማራበት የግዳጅ ቀጣና ሁሉ ህዝባዊ ባህሪውን በመላበስ እንዲሁም ራሱን በቴክኖሎጂ እየዘመነ የሕዝብን ደህንነት የማስከበር ኃላፊነቱን በከፍተኛ ደረጃ እየተወጣ ይገኛል።

ሌተናል ጄኔራል ሹማ አክለውም ዕዙ የኢትዮጵያን ሰላም በማጽናት፣ ታላላቅ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በመጠበቅ እና ሀገራችን እያካሄደች ያለችው የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያለ እንቅፋት እንዲቀጥል ለማስቻል ቀን ከሌት አክራሪ ፅንፈኞችን አሳዶ በመምታት ረገድ አጥጋቢ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ጠቁመዋል።

 በመሆኑም የፅናት ኮርስ ሰልጣኞች የቀይ መለዮ ባለአደራና ተተኪ መሆናቸውን በመገንዘብ፣ ቀሪ የስልጠና ጊዜያቸውን በእልህ፣ በወኔ፣ በጀግንነት እና በታታሪነት መከታተል እንደሚገባቸው በአጽንኦት አሳስበዋል።

የዕዙ ምክትል አዛዥ ሜጄር ጄኔራል አበባው ሰይድ በበኩላቸው፤ ሀገራችን ከትላንት እስከዛሬ በጀግኖች ልጆቿ ታፍራና ተከብራ የኖረች መሆኗን አንስተዋል።


ይህንን የቀደምት ጀግኖች ገድል ለማስቀጠል የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ የሚሰጠውን ሀገራዊና ተቋማዊ ግዳጅ ማናቸውም የአየር ንብረት መለዋወጥ፣ የውኃ ጥም እና ድካም ሳይበግረው በጀግንነት እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ሰልጣኞቹ በቀጣይ ባለ ቀይ መለዮ ለባሹን ዕዝ ሲቀላቀሉ ይህንን የጀግንነት ታሪክና አደራ ለማስቀጠል በአካልና በሥነ ልቦና ዝግጁ መሆን እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

የማሰልጠኛ ማዕከሉ አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ቦጃ አጋ በበኩላቸው ሰልጣኞቹ በስልጠና ሂደቱ ላይ እያሳዩት ስላለው የላቀ ተነሳሽነት እና ስለተመዘገበው ውጤት ማብራሪያ መስጠታቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ማሕበራዊ ድረ ገጽ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።