Search

የኢትዮጵያ አየር መንገድ - የቱሪዝማችን የጀርባ አጥንት

ዓርብ ሰኔ 26, 2018 76

ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ትኩረት ከሰጣቸው አምስት ዋና ዋና የኢኮኖሚ ምሰሶዎች መካከል ቱሪዝም ግንባር ቀደሙ ነው።

ይህንን ዘርፍ ከተለመደው የታሪክ ቅርስነት አልፎ ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚ ሞተርነት ለማሸጋገር፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እያበረከተ ያለው አስተዋጽዖ ከፍተኛ ነው፡፡

አየር መንገዳችን ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ ላለፉት ስምንት አሥርት ዓመታት በአፍሪካ የአቪዬሽን ታሪክ ተወዳዳሪ የሌለው መሪ ነው።

ከቅኝ አገዛዝ መክሰም ማግስት ጀምሮ አፍሪካውያንን ከዓለም ጋር በማገናኘት የሰውን ሠራሽ ድንበሮች የሰበረ የፓን-አፍሪካዊነት ታላቅ ተምሳሌትም ነው።

ዛሬም "የአፍሪካ ኩራት" እና "የአፍሪካ አዲስ መንፈስ" የሚሉትን መርሆዎቹን በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል።

በሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማሳደግ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ እያፈሰሰ የሚገኘው አየር መንገዳችን፣ ለዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢቶች እና ለቱሪስት አስጎብኚ ድርጅቶች ከሚያስፈልገው ጠቅላላ በጀት ውስጥ እስከ 25 በመቶ የሚሆነውን በራሱ ይሸፍናል፡፡ ይህም ለሀገራዊ ኢኮኖሚው ትንሣኤ ያለውን ጥልቅ ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።

አየር መንገዱ፣ የቱሪዝም ሚኒስቴር እና የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ጋር በመተባበር ታሪካዊ ስምምነት ተፈራርመዋል።

በዚህም የትራንዚት መንገደኞች 24 ሰዓት እስከ 7 ቀናት ለሚደርስ ቆይታ ያለ ቪዛ ክፍያ ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው ኢትዮጵያን መጎብኘት ይችላሉ፡፡

ይህ ማለት መንገደኞች በአንድ የአየር ትኬት ሁለት ሀገር የመጎብኘት "ጉርሻ" ያገኛሉ ማለት ነው።

8 እስከ 24 ሰዓታት የትራንዚት ጊዜ ያላቸው መንገደኞች ደግሞ ያለምንም ተጨማሪ የአየር በረራ ክፍያ ሆቴል አርፈው የኢትዮጵያን ቡና እየጠጡ እንዲያርፉ ይደረጋል።

ለዚህም በአፍሪካ ግዙፍ ከሚባሉት ተርታ የሚሰለፈው እና 1 ሺህ 24 ክፍሎች ያሉት ዘመናዊው የኢትዮጵያ ስካይላይት ሆቴል እንዲሁም በአየር መንገዱ ውስጥ የሚገኘው ተርሚናል ሆቴል በከፍተኛ ደረጃ አገልግሎት እየሰጡ ነው።

ተጓዦቹ በአጭር ጊዜ ቆይታቸው ልዩ በሆኑ ፓኬጆች የእንጦጦ ፓርክን፣ የብሔራዊ ሙዚየምን (ድንቋን ሉሲን) የአንድነት ፓርክን እና የዓድዋ ድል መታሰቢያን ጎብኝተው ይመለሳሉ።

የቱሪዝም ትልቁ ማነቃቂያ ደግሞ አዳዲሶቹ "ገበታ ለሀገር" መዳረሻዎች ከአየር መንገዱ ጋር መተሳሰራቸው ነው።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) አነሳሽነት የተገነቡት ሐላላ ኬላ፣ የዝሆን ዳና፣ ወንጪ እና ጎርጎራ ሎጆች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ አስደናቂ ሥፍራዎች ናቸው።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የእነዚህን አራት ቁልፍ ሎጆች አስተዳደር ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ (በስካይላይት ሆቴል ብራንድ ሥር) አስረክቧል።

ይህ ማለት፣ አንድ ቱሪስት አውሮፕላን ውስጥ ከገባበት ሰዓት ጀምሮ እስከ እነዚህ ገነት መሳይ ሎጆች ድረስ ወጥ የሆነ፣ የኢትዮጵያውያንን ሞቅ ያለ የእንግዳ ተቀባይነት የሚያንጸባርቅ አገልግሎት ያገኛል ማለት ነው፡፡

ይህን አኅጉራዊ እና ሀገራዊ ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር አየር መንገዱ በነገሌ ቦረና፣ በጎሬ መቱ እና በደብረ ማርቆስ አዳዲስ የሀገር ውስጥ አውሮፕላን ማረፊያዎችን ገንብቶ አገልግሎት ጀምሯል።

እነዚህ ማረፊያዎች የትራንስፖርት መስመሮች ብቻ ሳይሆኑ፣ የሀገራችንን ድንቅ የተፈጥሮ እና የታሪክ ሀብቶች ለዓለም የሚገልጡ አዳዲስ የቱሪዝም በሮች ናቸው፡፡

አየር መንገዳችን ኢትዮጵያን መጎብኘት አሁን ከመቼውም ጊዜ በላይ ቀላል እና ማራኪ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

በለሚ ታደሰ