Search

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ፡ ለኢኮኖሚ ብልጽግና የተጣለ የዘመናዊነት መሠረት

ዓርብ ሰኔ 26, 2018 38

 የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ከተመሰረተበት ከታኅሣሥ 2014 . ጀምሮ ሀገራዊ የኢኮኖሚ መልክን በመቀየር ላይ ይገኛል።

ተቋሙ በተበታተነ አሠራር ይተዳደሩ የነበሩ ሀገራዊ ሀብቶችን እና የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን በአንድ ስልታዊ መዋቅር ስር በማሰባሰብ ታሪካዊ ለውጥ እያስመዘገበ ነው።

በሁለገብ ስኬቶቹም በባለቤትነት የያዛቸውን እና የሚመራቸውን ግዙፍ ብሔራዊ ንብረቶች በማሳደግ፣ የሆልዲንግሱ ጠቅላላ የሀብት መጠን 8.2 ትሪሊዮን ብር እንዲደርስ አድርጓል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) በተደጋጋሚ እንዳስገነዘቡት፣ የተቋሙ መመስረት ከሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ጋር ቀጥተኛ ትስስር ያለው ስልታዊ እርምጃ ነው።

ቀደም ሲል በነበረው የተዛባ የፋይናንስ አጠቃቀም እና ዘላቂነት በሌለው የውጭ እዳ የተተበተቡ የመንግሥት ፕሮጀክቶችን በማስተካከል ሀገራዊ ሀብትን ለቀጣዩ ትውልድ በክብር ለማስተላለፍ የሚያስችል የዘላቂ ሀብት ማፍሪያ ሆኖ ተቀርጿል።

ይህ መዋቅራዊ ለውጥ ኢትዮጵያ የግል ዘርፉን ወደሚያስቀድም የኢኮኖሚ ሥርዓት የምትሸጋገርበት "መደመር" ፍልስፍና ዋነኛ መገለጫ ነው።

የልማት ድርጅቶችን ከኪሳራ በማዳን እና የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ረገድ እጅግ ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል።

ተቋሙ ተግባራዊ ባደረጋቸው ጠንካራ የአመራር እና ቁጥጥር ስልቶች ድርጅቶቹ በፍጥነት ወደ ትርፋማነት እንዲሸጋገሩ አድርጓል።

ለዚህም እንደ ማሳያ 52 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ዓለም አቀፍ ተደራሽነትን ማረጋገጥ መቻሉ ለሀገራችን የውጭ ምንዛሪ አቅም ግንባታ ትልቅ ምሰሶ ሆኗል።

ከዚህ ባለፈም 3.9 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በመሳብ እንዲሁም 297 ሺህ 532 ኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል በመፍጠር ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን አረጋግጧል።

በአስተዳደር ረገድም የቦርድ አባላት ክፍያን ከድርጅቱ ትርፋማነት እና ከኦዲት ውጤት ጋር በማስተሳሰር ግልጽ የተጠያቂነት አሠራርን አስፍኗል።

ድርጅቶች ከመንግሥት ጥገኝነት ወጥተው ራሳቸውን እንዲችሉ የሚያግዝ ስልታዊ የሪፎርም ሥራ በመሠራቱ እንደ ኢትዮ-ፖስታ ያሉ አንጋፋ ተቋማት ገቢያቸውን በእጅጉ ማሳደግ ችለዋል።

በኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ምስረታ ሂደት ውስጥ ግንባር ቀደም ተዋናይ በመሆን በሀገራችን የካፒታል ገበያ እውን እንዲሆን አድርጓል።

በቶፓን ግራቪቲ የጋራ ማኅበር አማካኝነት የፓስፖርት ህትመትን በሀገር ውስጥ በማከናወንም የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ርምጃ ወስዷል።

የፓስፖርት ሕትመቱ ከቴክኖሎጂ ሽግግር ባለፈ የዜጎችን ምስጢራዊ መረጃ በመጠበቅ ለሀገር ደኅንነት ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ትልቅ እርምጃ ነው፡፡

በዚህም መሰረት ተቋሙ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከማዘመን ባለፈ፣ ለወደፊቱ የኢትዮጵያ ብልጽግና እጅግ አስተማማኝ መሠረት ጥሏል።

በለሚ ታደሰ