በኢትዮጵያ ረጅም የታሪክ ጉዞ ውስጥ፣ እያንዳንዱ ዘመን የራሱ የሆነ የክብር ጥሪ እና የትውልድ ግዴታ ይዞ ብቅ ይላል።
ታሪካችንን ወደኋላ መለስ ብለን ስንመረምር፣ የትናንቱ አባቶቻችን እና እናቶቻችን የተጠሩት ኢትዮጵያን ከጠላት እና ወራሪ ጠብቆ የማቆየት ትውልዳዊ ተልዕኮን የመወጣት ኃላፊነት ላይ ነበር።
ደሙን አፍሶ እና አጥንት ከስክሶ ከባሕር ማዶ ማዕበልን ሰንጥቆ የመጣን ወራሪ ኃይል፣ እስከ መመለስ ድረስ የነበረው ዘመን - የነጻነት እና የጦር ሜዳ ዐርበኝነት ዘመን ነበር። ያ ትውልድ ሀገር እንዳትደፈር፣ ሉዓላዊነቷ እንዳይነካ፣ ባንዲራዋም ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ፣ በቅኝ ግዛት ሥር ሀገር እንዳትወድቅ ታሪካዊ ግዴታውን በጀግንነት ተወጥቷል፤ ዐሻራውንም በደሙ ጽፎልን አልፏል።
ዘመን ዘመንን ሲተካ፣ የታሪክም ሆነ የዐርበኝነት ትርጉም አዲስ እና ወቅታዊ መልክ ይይዛል። የዛሬው ዘመን ዐርበኝነት በጦር ሜዳ ላይ ብቻ የሚፈጸም ሳይሆን፣ ኢትዮጵያን ከኋሊት ጉዞ በመመለስ ከጥልቅ ድህነት አውጥቶ በብልጽግና ማማ ላይ የማስቀመጥ የኢኮኖሚ እና የሥነ ልቦና ዐርበኝነት ሆኗል።
ይህ የዛሬው ትውልድ ሀገሩን በልማት የማነጽ፣ በቴክኖሎጂ የማዘመን እና ዜጎቿን ቀና አድርጎ የማስኬድ ከባድ፣ ግን ደግሞ ክቡር ታሪካዊ ኃላፊነት ትከሻው ላይ ወድቋል።
ነገር ግን፣ ይህንን የዕድገት እና የብልጽግና ጉዞ በከፍተኛ ሁኔታ የሚያደናቅፍ፣ ለዘመናት የሀገራችንን ኢኮኖሚ እያዳሸቀ እና እያንገዳገደ የሚገኝ አንድ ትልቅ ስትራቴጂያዊ ማነቆ አለ።
እርሱም የባሕር በር አልባነት፣ የውጭ ወደብ ኪራይ ጥገኝነት እና ከዚህ ሁሉ የሚመነጨው የሉዓላዊነት ጫና ነው። መተንፈሻዋ የታፈነባት፣ ወጪ እና ገቢ ንግዷ በሌሎች ሀገራት በጎ ፈቃድ ላይ ብቻ የተንጠለጠለች ኢትዮጵያ፣ የቱንም ያህል በውስጥ አቅሟ ብትተጋም የተሟላ የኢኮኖሚ ነጻነትን እና ብልጽግናን ማምጣት እንደማትችል እሙን ነው።
ይህንን መራራ እና አስገዳጅ እውነት በሚገባ የተረዳው የዘመኑ ትውልድ፣ አዲስ የትግል መንፈስ አርግዟል። እነሆ ከዚህ ጥልቅ ሀገራዊ ቁጭት እና ንቃት፣ የቀይ ባሕር ዐርበኛ ትውልድ በይፋ ተወልዷል!
ይህ ትውልድ የኢትዮጵያን ጂኦ-ፖለቲካዊ ዕጣ ፈንታ ለዘለዓለሙ ለመቀየር የተነሣ የብሩህ አዕምሮ ባለቤት ነው።
የቀይ ባሕር ዐርበኝነት፣ ትናንት በጦር ሜዳ እንደተደረገው ደም አፋሳሽ ተጋድሎ ሁሉ፣ ዛሬ ደግሞ የኢትዮጵያን የተፈጥሮ እና የታሪክ መብት ለማስመለስ የሚደረግ የሠለጠነ ተጋድሎ ነው።
የሀገራችንን ኢኮኖሚያዊ አንገት ከኪራይ ቀንበር ነጻ ለማውጣት፣ እና የታፈነውን መተንፈሻ ወለል አድርጎ ለመክፈት የሚደረግ የዕውቀት፣ የዲፕሎማሲ እና የጽናት ዘመቻ ነው።
ይህ የቀይ ባሕር ዐርበኛ ትውልድ ዛሬ ላይ አንድ ጽኑና የማይናወጥ የጋራ ስምምነት ላይ ደርሷል። በአንድ ልብ፣ በአንድ ድምፅ "ቀይ ባሕር ተፈጥሯዊ ደጃፋችን፣ ታሪካዊ ወደባችን ነው!" በማለት አውጇል።
ይህ ስምምነት የፖለቲካ ትኩሳት የወለደው ጊዜያዊ ስሜት፣ ወይም የቅንጦት ምኞት አይደለም። ይልቁንም በጥልቅ የጂኦ-ፖለቲካ ንባብ፣ በታሪክ ግንዛቤ እና በኢኮኖሚ ሕልውና አስገዳጅነት ላይ የተመሠረተ ጽኑ አቋም ነው።
የቀይ ባሕር ዐርበኛ ትውልድ አሮጌውን የጥገኝነት ትርክት ሰብሮ፣ አዲስ የነጻነት አየር ለመተንፈስ ቆርጦ ተነሥቷል።
እውነትም ይህ ትውልድ የተመኘውን ያገኛል፤ የታለመበትን የክብር ቦታ ይደርሳል! ያኮረፈውን የባሕር ሞገድ ታርቆ፣ የኢትዮጵያን የጥንት ክብር እና ልዕልና በገዛ ደጃፏ ላይ ዳግም ይመልሳል።
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ