ዛሬ ኢትዮጵያ የምትገኝበት ወቅታዊ ሁኔታ አንድ ወርቃማ መርህን እንድንይዝ ያስገድደናል፤ እሱም “በውይይት ብቻ የምትጸና ሀገር” የሚለው ነው።
ታሪክን በኃይል ለመጻፍ፣ ልዩነቶችን በጠብመንጃ ለመፍታት የተደረጉ ጥረቶች ሁሉ ሀገራችንን ዋጋ አስከፍለዋል እንጂ አላጸኑም።
በመሆኑም፣ አሁን ላይ የተጀመረው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም፣ ለሰለጠነ ፖለቲካ እና ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ብቸኛው እና አማራጭ የሌለው መንገድ ነው።
ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚለቀቁ የጥላቻ ንግግሮች እና የፖለቲካ ቁርሾዎች የሚመነጩት ካልተፈቱ የታሪክ ጠባሳዎች እና ካልተደመጡ ብሶቶች መሆኑ ይታወቃል።
ኢትዮጵያ እያከናወነች የምትገኘው ሀገራዊ ምክክሩ ሁሉንም ወገኖች፣ የታጠቁትንም ሆነ የሲቪክ ማኅበራትን፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እና ተራውን ዜጋ በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ በማስቀመጥ የበደል ታሪኮችን በሰለጠነ መንገድ ለመነጋገር ብቸኛው መድረክ ነው።
ቂም በቀል የሚቆመው እና ዘላቂ ሰላም የሚረጋገጠውም ሁሉም ወገን በነጻነት ተደምጦ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ሲቻል ብቻ ነው።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ትልቁ ክፍተት የውይይት እና የሰለጠነ ክርክር ባህል ማነስ ነው።
ፖለቲካ ማለት የጠላትነት እና የሴራ ሜዳ ሳይሆን፣ የሐሳብ እና የውሳኔ ጥበብ መሆን ይጠበቅበታል።
የሀገራዊ ምክክሩ ሂደት አካታችነትን በማስፈን አግላይ ያልሆነ እና የሁሉንም ድምጽ የሚያከብር መድረክ ይፈጥራል፡፡
መቻቻል የልዩነት ውበት እንጂ የጥፋት መነሻ አለመሆኑን በተግባር ያስተምራል። እንዲሁም የፖለቲካ ሥልጣን በሕዝብ ይሁንታ እና በውይይት እንጂ በኃይል እንደማይገኝ ያረጋግጣል።
አንድ ሀገር ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ሊኖር የሚችለው ዜጎቿ በጋራ በሚስማሙበት የሀገር ምስረታ ትርክት ሕገ-መንግሥታዊ መርሆዎች እና ብሔራዊ ምልክቶች ላይ የጋራ መግባባት ሲኖራቸው ብቻ ነው።
በኢትዮጵያ ላለፉት አሥርት ዓመታት የቀጠለው አለመረጋጋት መሠረቱ ይኸው የጋራ ትርክት ማጣት ነው።
ሀገራዊ ምክክሩ በታሪካችን፣ በጋራ እሴቶቻችን እና በወደፊት እጣ ፈንታችን ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ፣ የመተማመኛ ምሰሶዎችን ይተክላል። ይህም ለሚገነባው ጠንካራ ሀገረ መንግሥት እንደ ማዕዘን ድንጋይ ያገለግላል።
በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቻችን ላይ የምንሰነዝረው እያንዳንዱ ቃልም ሆነ የምናጋራው እያንዳንዱ ቪዲዮ ውይይትን የሚያበረታታ ወይስ ግጭትን የሚቀሰቅስ? ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል።
ስለሆነም፣ ይህ ሂደት እንዲሳካ፣ የሐሳብ ልዩነቶች በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ እና በውይይት የምትጸና ሀገር እንድትገነባ ሁላችንም በያለንበት የበኩላችንን አዎንታዊ ሚና ልንወጣ ይገባል።
በአድማሱ አራጋው