Search

የዜጎችን አኗኗር እና የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጠው አዲሱ የልማት ስትራቴጂ

ዓርብ ሰኔ 26, 2018 63

 

የኢትዮጵያ አዲሱ የልማት ጉዞ መሠረቱን ወደ ገጠሩ ማኅበረሰብ በማዞር ለዘመናት የዘለቀው የገጠር አኗኗር ዘይቤ በከፍተኛ ፍጥነት እየተቀየረ ይገኛል።

ይህ ስትራቴጂያዊ የልማት መንገድ በከተሞች የታየውን ውጤታማ የኮሪደር ልማት ተሞክሮ እና ፈጣን የአፈፃፀም ባህል ወደ ገጠሩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በማሸጋገር አርሶ አደሩን የዘመናዊ መሠረተ-ልማት እና የተሟላ ሰብዓዊ ክብር እንዲኖረው እያደረገ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ትናንት ያስመረቁት ዘመናዊው የሀማሳ ሞዴል መንደር የመሳሰሉ የገጠር ኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች፣ በተበታተነ እና በባህላዊ መንገድ ይኖር የነበረውን ማኅበረሰብ ወደተደራጀና ምቹ አኗኗር በማሸጋገር የለውጡን ፍሬ በተግባር ያሳየ ሆኗል።

የዚህ አዲስ የልማት መንገድ ዋነኛው ስኬት፣ የገጠሩን ማኅበረሰብ ከያዘው ኋላ ቀር እና አድካሚ የአኗኗር ዘይቤ ማውጣት መቻሉ ላይ ነው።

ልማቱ ንፁህ የመታጠቢያ ክፍሎችን፣ ዘመናዊ የቤት አቀማመጦችን፣ የተሻሻሉ የእንስሳት ማደሪያዎችን እና የባዮ ጋዝ የኃይል አማራጮችን ወደ ገጠር መንደሮች በስፋት በማስገባት የአርሶ አደሩን የኑሮ ጥራትና ምቾት ወደ ላቀ ደረጃ አሳድጎታል።

ይህ አሠራር ማኅበረሰቡ ከንፅህና መጓደልና ከባህላዊ አኗኗር ጫና ተላቅቆ ጤናው የተጠበቀ እና በራሱ የሚተማመን ዘመናዊ አምራች ኃይል ሆኖ እንዲቀረጽ ትልቅ የማኅበራዊ እሴት ለውጥ ፈጥሯል።

የገጠር ኮሪደር ልማት የአኗኗር ዘይቤን ከመቀየር ጎን ለጎን የሀገራችን የጀርባ አጥንት የሆነውን የምግብ ዋስትና በዘላቂነት ለማረጋገጥ የተዘረጋ ዋነኛ የኢኮኖሚ ሞተርም ጭምር ነው።

ፕሮጀክቱ አርሶ አደሩ ከመደበኛው የሰብል ምርት ባለፈ የተቀናጁ የአትክልት ስፍራዎችን፣ ዘመናዊ የንብ ቀፎዎችን እና የዶሮ እርባታዎችን በአንድ ግቢ ውስጥ እንዲያደራጅ በማድረግ የምግብ እና የሥርዓተ ምግብ ዋስትናውን በማረጋገጥ ከራሱ ለሌሎችም እንዲተርፍ ያስችለዋል።

ይህ ሁለንተናዊ የምርታማነት ዕድገት አርሶ አደሩን ከዝናብ ጥገኝነት እና ከዕለት እርዳታ ሙሉ በሙሉ በማውጣት በምግብ ራሱን የቻለ እና ለሌላው በመትረፍ ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚያቀርብ ጠንካራ የኢኮኖሚ ምሰሶ እያደረገው ይገኛል።

በሃና ምንዳሁን