ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት አዳዲስ የቱሪዝም መንደሮችን በመገንባት እና የቱሪስት መዳረሻዎቿን በማስፋት ዘርፉን የኢኮኖሚዋ ዋነኛ ምሰሶ ለማድረግ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገች ትገኛለች።
የዚህ ሀገር አቀፍ ስትራቴጂ ስኬት ደግሞ ያለ መሠረተ-ልማት ግንባታ ፈፅሞ የማይታሰብ ነው።
በአሁኑ ወቅት በጥሩ አፈጻጸም ላይ የሚገኘው የጫኖ-ጨንቻ የመንገድ ፕሮጀክት የዚህ ጥሩ ማሳያ ነው።
22 ኪሎ ሜትር የጫኖ-ጨንቻ ዋና መስመር እና 7 ኪሎ ሜትር የኤዞ-ጊርጫ ቅርንጫፍ መንገድን ካካተተው የ29 ኪሎ ሜትር ፕሮጀክት ላይ እስካሁን 13.3 ኪሎ ሜትር የሚሆነው ተጠናቅቋል።
ፕሮጀክቱ መንግሥት የጀመረው የቱሪስት መዳረሻዎችን በመንገድ መሠረተ-ልማት የማስተሳሰር ሥራ አካል ሲሆን፣ ይህም ወደ ስፍራው ለመጓዝ የሚወስደውን ጊዜ በማሳጠር የቱሪስት ፍሰትን በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራል።
ሀገራችን በቱሪዝም ልማት ዘርፍ ከምትከተላቸው ስልቶች አንዱ ማህበረሰቡን ባለቤት ማድረግ እና ባህልን ከተፈጥሮ ጋር ማቀናጀት ነው።
ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ በማህበረሰቡ ጠንካራ ባለቤትነትና መሪነት ተገንብቶ፣ በቅርቡ አዲስ መልክ የያዘው የዶርዜ ሎጅ የዚህ ማህበረሰብ-ተኮር የቱሪዝም ልማት ሕያው ማሣያ ነው።
በቀዝቃዛና ሰንሰለታማ ጋራ፣ በ40 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈው ይህ አስደናቂ ሥፍራ፣ የአባያና ጫሞ ሐይቆችን ውበት እንዲሁም “የእግዜር ድልድይ” የተባለውን የተፈጥሮ ድንቅ ሥራ በአንድ ላይ አጣምሮ ይዟል።
ይህን የመሰሉ ውብና ዘመናዊ መዳረሻዎች መገንባታቸው ኢትዮጵያ በዘርፉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተወዳዳሪነት ከፍ የሚያደርግ ነው።
ኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻዎቿን በማልማት የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ባህልን እና የውጭ ምንዛሬ ግኝቷን ለማሳደግ በምታደርገው ጥረት፣ እንደ ዶርዜ ሎጅ ያሉ መስህቦች ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል።
ዘመናዊ የመንገድ መሠረተ-ልማት መዘርጋቱ በአካባቢው ያለውን የኢኮኖሚና የባህል እምቅ አቅም አሟጦ ለመጠቀም ዕድል ፈጥሯል።
በመሆኑም፣ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም በመላው ዓለም የሚገኙ ቱሪስቶች ይህን የበለጸገ የተፈጥሮ ውበትና የባህል ሐብት እንዲጎበኙና የታሪኩ ተጋሪ እንዲሆኑ ጥሪ ቀርቧል።
መጪው ጊዜ የአካባቢው ማህበረሰብ ከቱሪዝም ልማቱ ተጠቃሚነቱ የሚረጋገጥበት ብሩህ ጊዜ ይሆናል።
በሔዋን ጌታቸው