Search

የኢትዮጵያ ቱሪዝም አዲሱ መልክ፡- ከታሪካዊ ስፍራዎች እስከ ‘ገበታ’ ፕሮጀክቶች

ዓርብ ሰኔ 26, 2018 67

 ኢትዮጵያ ረጅም ዘመናት ያስቆጠሩ የታሪካዊ፣ ባህላዊ እና ተፈጥሯዊ ሀብቶች ባለቤት ብትሆንም፣ የቱሪዝም ዘርፉን ወደ ላቀ የኢኮኖሚ እና የገጽታ ግንባታ ምሰሶነት ለመቀየር ስትራቴጂያዊ ሽግግር የግድ አስፈላጊ ሆኖ ቆይቷል።

ዛሬ ላይ ሀገራችን የያዘችው አዲስ የቱሪዝም ስትራቴጂ፣ ዘርፉን ከባህላዊ የጉብኝት ዘይቤ በማውጣት ወደ ዘመናዊ፣ ዘላቂ እና ሁሉን-አቀፍ ልማት እያሸጋገረው ይገኛል።

ይህ ሽግግር የቱሪዝም መዳረሻዎችን ከማስፋፋት ባለፈ፣ የሀገራችንን ማክሮ-ኢኮኖሚ ለማጠናከር ታስቦ የተቀረጸ አዲስ ምዕራፍ ነው።

ቀደም ሲል በታሪካዊ የቱሪስት መስህቦች ላይ ብቻ የተንጠለጠለ ይመስል የነበረውን የኢትዮጵያ ቱሪዝም የለውጡ መንግሥት በተከተለው አዲሱ ስትራቴጂያዊ ሽግግር ሙሉ በሙሉ መቀየር ተችሏል።

በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የቱሪዝም ዘርፍ አንዱ የኢኮኖሚ ምሰሶ ተደርጎ መመረጡን ተከትሎ፣ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች በከፍተኛ ፍጥነትና ጥራት ማልማት ተችሏል።

በዚህም የገበታ ውጤቶች የሆኑት እንደ ጎርጎራ፣ ወንጪ፣ ኮይሻ እና ሌሎችም አዳዲስ ብሔራዊ ፕሮጀክቶች የሀገራችንን የተፈጥሮ እና የሥነ-ምህዳር ፀጋዎች ወደ እውነተኛ የቱሪስት መስህብነት ቀይሯቸዋል።

እነዚህ አዳዲስ መዳረሻዎች ተፈጥሮን፣ ስፖርትን፣ ባህልን እና ዘመናዊ መስተንግዶን በአንድ ላይ አጣምረው የያዙ በመሆናቸው የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኝዎችን የተለያየ ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ ማርካት ችለዋል።

አዲሱ የቱሪዝም ሽግግር በብቸኝነት የቆመ ሳይሆን፣ ከታላላቅ ብሔራዊ የመሠረተ-ልማት ግንባታዎች ጋር በጥብቅ የተቆራኘ መሆኑም ዘርፉን ይበልጥ ውጤታማ እያደረገው ይገኛል።

እንዲሁም በመዲናችን አዲስ አበባ የተከናወኑትና በሌሎች ከተሞች እየተስፋፉ የሚገኙ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች ለከተማ ቱሪዝም አዲስ መነቃቃትን ፈጥረዋል።

በዚሁም ንፁህ፣ ሳቢ እና ለእግር ጉዞ ምቹ የሆኑ መንገዶች፣ የከተማ መናፈሻዎችና የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች የቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም ትልቅ አስተዋፅዖ እያበረከቱ ነው።

ከዚህ ባለፈም ወደ አዲሶቹ የክልል የቱሪስት መዳረሻዎች የሚወስዱ የትራንስፖርት እና የዲጂታል መሠረተ-ልማቶች መዘርጋታቸው የጉዞ ተደራሽነትን እጅግ ቀላል እንዲሆን አስችሏል።

ይህ ስትራቴጂያዊ ሽግግር ከውበት እና ከገጽታ ግንባታ ባለፈ ጥልቅ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው ነው፡፡

በዚህም ኢትዮጵያ ከዕዳ-ተኮር ወደ ምርት እና አገልግሎት-ተኮር የኢኮኖሚ ስትራቴጂ በምታደርገው ጉዞ ቱሪዝም ዋነኛውን ድርሻ ይዟል።

በዚህም በውጭ ምንዛሪ ግኝት ከአገልግሎት ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ የማክሮ-ኢኮኖሚ መረጋጋትን መደገፍ፣ በኢኮ-ቱሪዝም እና በመስተንግዶ ዘርፍ ለወጣቶችና ለአካባቢው ማኅበረሰብ የሥራ ዕድል መክፈት፣ ከአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች እስከ ትላልቅ ሆቴሎች ያለውን ትስስር ማጠናከር ተችሏል።

የኢትዮጵያ ቱሪዝም አዲሱ ስትራቴጂያዊ ሽግግር የሀገራችንን የተፈጥሮ እና የታሪክ ፀጋዎች በአግባቡ ወደ ሀብት የመቀየር ታላቅ ራዕይ ነፀብራቅ ነው።

በዚህም በዘርፉ የተጀመረው አዲስ ምዕራፍ፣ ሀገራችንን በአፍሪካ ቀንድ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ቀዳሚና ተመራጭ መዳረሻ የማድረግ አቅም እንዳለው በተግባር እያሳየ ይገኛል።

በአድማሱ አራጋው