ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የልማት ሥራዎችን ማከናወኗን አጠናክራ እንደቀጠለች በመግለጽ፣ የ‘ገበታ ለትውልድ’ መርሃ-ግብር ያፈራውን ሌላኛውን ታላቅ ስኬት የሆነውን የአርባምንጭ ኮንፈረንስ ሪዞርትን ዛሬ በይፋ መርቀዋል።
ይህ አዲስ እና ዘመናዊ ሪዞርት ከ1 ሺህ 300 በላይ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል ሰፊ የስብሰባ አዳራሽ እና በሐይቅ ላይ የተገነባ ልዩ ተንሳፋፊ ሬስቶራንትን በውስጡ ያካተተ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳስታወቁት፣ ይህ ፕሮጀክት ከመዲናችን ባሻገር የኮንፈረንስ ቱሪዝምን በማስፋፋት ኢትዮጵያን የዓለም አቀፍ መድረኮች ማዕከል የማድረግ ርዕይን በከፍተኛ ደረጃ ያጠናክራል። ከዚህም በተጨማሪ ፕሮጀክቱ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልእክት፤ መላው የሀገራችን ሕዝብ፣ የዳያስፖራው አባላት እና የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ይህንን አዲስ የሀገራችንን ዕንቁ ስፍራ በመጎብኘትና በመጠቀም፣ የኢትዮጵያን አዲስ የቱሪዝምና የኮንፈረንስ ምዕራፍ በጋራ እንዲቋደሱ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።