Search

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ ጅኦ ፓርክ በዩኔስኮ ለማስመዝገብ የተደረገው ዝግጅት ተጠናቅቋል

እሑድ ሰኔ 28, 2018 76

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኘው የስልጤና ቡታጅራ ጂኦ-ፓርክ በዩኔስኮ ዓለም አቀፍ መዝገብ ውስጥ እንዲሰፍር የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸውን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታውቋል።

የቱሪዝም ሚኒስቴር እና የዩኔስኮ የአዲስ አበባ ቢሮ ተወካዮችን የያዘው ልዑካን ቡድን በስፍራው በመገኘት ባደረገው የመስክ ምልከታና የማረጋገጫ ሥራ ፓርኩ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) መመዘኛዎች የማሟላት አቅምን አረጋግጧል።

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ እንደገለጹት፣ የስልጤና ቡታጅራ አካባቢ ጆኦ ፓርክ የኢትዮጵያ የመጀመሪያው የዩኔስኮ ጂኦ-ፓርክ እንዲሆን ባለፉት ሁለት ዓመታት ሰፊ ጥናታዊ ሥራዎች ተከናውነዋል።

የፓርኩን የጂኦሎጂ ሀብትና የምድር አፈጣጠር ታሪክ በተመለከተ እንደ ፕሮፌሰር አስፋውሰን ያሉ ታዋቂ የኢትዮጵያ ጂኦሎጂስቶች ዓለም አቀፍ ጥናቶችን አጥንተው እንዲታተሙ መደረጋቸውና የዩኔስኮ የዶሴ ሰነዶችን የማዘጋጀትና የማሳተም ሥራ መጠናቀቁ ተገልጿል።

ልዑካን ቡድኑ የጂኦ-ፓርኩን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ከሚጠየቁ ዋነኛ መስፈርቶች መካከል የአካባቢው ማኅበረሰብ ሙሉ ድጋፍና ፈቃድ ማግኘት የባህል፣ የታሪክና የተፈጥሮ ውኅደትን ማረጋገጥ እንዲሁም በስምጥ ሸለቆ አካባቢ የሚገኙ የጥናት መረጃዎችን በአግባቡ ማደራጀት መጠናቀቃቸውን አረጋግጧል።

በተጨማሪም ቱሪስቶችን ለመቀበል የሚያስችሉ መረጃ ሰጪ ማዕከላት፣ አቅጣጫ ጠቋሚ ምልክቶች፣ ቢልቦርዶችና የመረጃ ፓናሎች ጨምሮ ዘመናዊ መሠረተ ልማቶች ተገንብተው መጠናቀቃቸው ተመላክቷል።

በክልሉ የሚገኙ እንደ ሀምበሪቾ ኢኮ ቱሪዝም፣ የጥያ ትክል ድንጋይ፣ የሃረሸታ ሐይቅና የዘቢዳር ተራራ ያሉ እምቅ የቱሪስት መዳረሻዎች የቱሪዝም ዘርፉን በኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ ያለውን ድርሻ ከፍ እንደሚያደርጉት ተገልጿል።

እነዚህን መዳረሻዎች በማልማት የሆስፒታሊቲ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ በትኩረት እየተሠራ መሆኑ መገለጹን ከቱሪዝም ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።