ለብዙ ዘመናት ገጠር በድህነት፣ በመሠረተ ልማት እጥረት እና በዘመናዊ አገልግሎቶች እጦት የሚገለጽ ስፍራ እንደሆነ ይታሰብ ነበር።
ዛሬ ግን ይህ አመለካከት በብዙ የዓለም ሀገራት የተቀየረ ሲሆን፣ ገጠር ከከተማ ያልተናነሰ የሕይወት ጥራት፣ ውብ መኖሪያ፣ ንጹህ አካባቢ እና ዘመናዊ አገልግሎቶች የሚገኙበት ስፍራ ሆኗል።
የተሳካላቸው ሀገራት ገጠርን እንደ ችግር አላዩትም፤ እንደ ዕድል በመቁጠር የአርሶ አደሩን ሕይወት ለመቀየር ቤት፣ መንገድ፣ ንጹህ ውኃ፣ መብራት፣ የጤና እና የትምህርት ተቋማት ከማሟላት ጀምሮ የገጠርን ገጽታ ሙሉ በሙሉ ቀይረዋል።
በቻይና የተካሄደው የገጠር ልማት የዓለም ትኩረት የሳበ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ድህነት ውስጥ የነበሩ መንደሮች ዛሬ ንጹህ መንገዶች፣ ዘመናዊ መኖሪያዎች፣ የቱሪዝም መዳረሻዎች እና የአካባቢ ኢኮኖሚን የሚያንቀሳቅሱ ማዕከላት ሆነዋል።
መንግሥት መሠረተ ልማትን ሲያሟላ ነዋሪዎች ደግሞ አካባቢያቸውን በመጠበቅ እና በማስዋብ ለለውጡ አጋር ሆነዋል።
ደቡብ ኮሪያም በ"ሴማኡል ኡንዶንግ" የተባለው የገጠር ልማት እንቅስቃሴ የገጠርን ሕይወት በእጅጉ ቀይራለች።
የተሻሉ ቤቶች፣ ንጹህ አካባቢዎች፣ የገጠር መንገዶች እና የጋራ ሥራ ባህል የአርሶ አደሮችን ገቢ እና ኑሮ አሻሽለዋል።
በአውሮፓ ደግሞ እንደ ኔዘርላንድስ፣ ስዊዘርላንድ እና ዴንማርክ ያሉ ሀገራት ገጠርን ከግብርና ማዕከልነት በላይ ወደ ውብ የመኖሪያ እና የቱሪዝም መዳረሻነት ቀይረውታል።
በእነዚህ ሀገራት ገጠር መኖር የከተማ ሕይወትን ከመከተል ያነሰ አይቆጠርም። የአካባቢ ውበት፣ የአረንጓዴ ልማት እና ዘላቂ አኗኗር የእነዚህ ሀገራት መለያ ሆኗል።
እነዚህ ሁሉ ተሞክሮዎች የሚያስተምሩን አንድ እውነት አለ። ገጠርን ማዘመን ማለት ሕንፃ መገንባት ብቻ አይደለም፤ የሰውን ሕይወት፣ የሥራ ባህልን፣ የአካባቢ ንጽህናን እና የወደፊት ተስፋን መቀየር ነው።
ዛሬ ኢትዮጵያም በዚህ አቅጣጫ ጉልህ እርምጃ እየወሰደች ትገኛለች። የተጀመረው የገጠር ኮሪደር ልማት ፕሮግራም የገጠር አካባቢዎችን ንጹህ፣ ውብ፣ ምቹ እና ዘመናዊ ለማድረግ ያለመ ነው።
የገጠር መንገዶች መሻሻል የመጠጥ ውኃ አቅርቦት መስፋፋት፣ የአካባቢ ጽዳት ባህል መጎልበት፣ የዛፍ ተከላ እና የመኖሪያ አካባቢዎች ውበት መጨመር በብዙ አካባቢዎች የሚታይ ለውጥ እየፈጠረ ነው።
በተለይ የንጽህና፣ የአረንጓዴ ልማት እና የማኅበረሰብ ተሳትፎ ላይ የተመሰረተው ይህ አካሄድ ገጠርን ለመኖር የሚፈለግ ስፍራ ለማድረግ የሚያስችል ነው።
የአርሶ አደሩ ልጅ በንጹህ አካባቢ እንዲያድግ፣ አምራቹ ምርቱን በቀላሉ ወደ ገበያ እንዲያደርስ እና ገጠር ከከተማ ያልተናነሰ የሕይወት ጥራት እንዲኖረው መሠረት እየተጣለ ነው።
ወደፊቷ ኢትዮጵያ በከተሞች ብቻ የምትገነባ አይደለችም። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች በሚኖሩባቸው ገጠራማ አካባቢዎች የሚፈጠረው ለውጥ የኢትዮጵያን ነገ ይወስናል።
ዓለም ያሳየው ተሞክሮ አንድ ነው፤ ከተማን ማዘመን ብቻ በቂ አይደለም፤ ገጠርን ማዘመን ነው ዘላቂ ልማትን የሚያረጋግጠው።
ኢትዮጵያም ዛሬ የጀመረችው የገጠር ኮሪደር ልማት በቀጣይነት ንጹህ፣ ውብ፣ ዘመናዊ እና ምርታማ የገጠር ማህበረሰብ የመፍጠር አቅሙ ከፍተኛ ነው።
ይህ ደግሞ የገጠርን ገጽታ ብቻ ሳይሆን የመላውን ሀገር ገጽታ የሚቀይር ለውጥ እንደሆነ በግልጽ እየታየ ነው።
በሀብተሚካኤል ክፍሉ