Search

ባገኘነው ዕውቀት ዓለም አቀፍ ስትራቴጂያዊ ዕይታን በመጠቀም ሀገራችንን ለማገልገል ተዘጋጅተናል - ተመራቂዎች

እሑድ ሰኔ 28, 2018 81

ያገኘነው ዕውቀት ዓለም አቀፍና ቀጣናዊ ስትራቴጂያዊ ዕይታን በተሻለ መንገድ እንድንረዳው አድርጎናል፤ ይህን ተጠቅመን ሀገራችንን ለማገልገል ተዘጋጅተናል ሲሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ኮሌጅ ተመራቂዎች ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ኮሌጅ በመከላከያና ስትራቴጂክ የደኅንነት ጥናት መስክ ሲያሰለጥናቸው የቆየውን ተመራቂዎች አስመርቋል።

ተመራቂዎቹ እንደገለጹት፣ በኮሌጁ በነበራቸው ቆይታ የተሰጣቸው ሥልጠና ዓለም አቀፍና ቀጣናዊ ስትራቴጂካዊ ዕይታን በከፍተኛ ደረጃ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል።

የኢፌዴሪ አየር ኃይል 3 አየር ምደብ ምክትል አዛዥ እና የተዋጊ ሄሊኮፕተር አብራሪና አስተማሪ ኮሎኔል ደረስ እንዳለ እንዳሉት፣ በኮሌጁ ያካበቱት እውቀት ኢትዮጵያ ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶችን በግልጽ ለመረዳትና ለመተንተን የሚያስችል ከፍተኛ አቅም ፈጥሮላቸዋል።

በተለይም ኢትዮጵያ የምትገኝበት የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያለውን ተለዋዋጭ ሁኔታ በውል ለመረዳት ማስቻሉን ገልጸው፣ ይህንን ስትራቴጂያዊ ዕይታ መሠረት በማድረግ ሀገራቸው የምትሰንቀውን ታላቅ ህልምና ግብ ለማሳካት በቁርጠኝነት ለመሥራት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አብራርተዋል።

ሌላው አስተያየታቸውን የሰጡት ሌተናል ኮሎኔል ቴዎድሮስ ገብረ ሩፋኤል (/) በበኩላቸው፣ በስትራቴጂክና ደኅንነት ጉዳዮች ላይ የተከታተሉት ትምህርት ዘርፈ-ብዙ ሁኔታዎችን በጥልቀት ለመተንተን ከፍተኛ እገዛ ማድረጉን ጠቁመዋል።

የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ተለዋዋጭ ሁኔታዎች የበዙበት መሆኑን አመልክተው፣ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በትብብር መንፈስ የሚንቀሳቀሱ ከሆነ የሚከናወኑ ተግባራት በሙሉ በጎ ውጤት እንደሚያስገኙ አመልክተዋል።

ሌላው ሰልጣኝ አቶ ጌታሰው ደሴ ሥልጠናው ለሀገር አንድነት እና ለተቋማት ግንባታ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ አስተዋጽኦ ለማበርከት ትልቅ አቅምና ወደፊት ለሚሰማሩበት የሥራ መስክም ስንቅ እንደሆናቸው ገልጸዋል።

በተመሳሳይ አስተያየታቸውን የሰጡት ሌተናል ኮሎኔል ደረጀ ዳባሳ ያገኙት ዕውቀት የዕለት ተዕለት ተግባራቸውና ከሙያቸው ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት ያለው በመሆኑ ስትራቴጂያዊ አካባቢውን፣ ጂኦፖለቲካውን እና አጠቃላይ ሁኔታውን በተገቢው መንገድ ለመረዳት እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።

ትምህርቱ ለተግባራዊ ሥራቸው ጠንካራ መነሻ ከመሆኑም በላይ፣ ባላቸው የረጅም ጊዜ ልምድ ላይ ትልቅ አቅም የገነባ መሆኑንም አክለዋል።

የኮሌጁ ሰልጣኝ የሆኑት ኮሎኔል እማምር አያሌው ቀጣናዊና የአካባቢውን ነባራዊ ሁኔታ በደንብ በመረዳት መተንተን የሚችል ጠንካራ ሠራዊት እየተገነባ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም በአስተሳሰብ የበሰለ፣ በስትራቴጂካዊ እውቀት የዳበረና ለማንኛውም ሀገራዊ ግዳጅ ዝግጁ የሆነ ሠራዊት እንደተገነባ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡