Search

የባሕር በር ከኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ባሻገር ለቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት ያለው አስተዋጽዖ

እሑድ ሰኔ 28, 2018 70

የዓለም አቀፍ የቱሪዝም መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፣ ከዓለም አቀፍ የቱሪስት ፍሰት እና ገቢ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በባሕር ዳርቻ ቱሪዝም ላይ የተመሰረተ ነው።

ይህ እውነታ ደግሞ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት በዘርፉ ላይ ያላቸውን ተወዳዳሪነት ከፍተኛ ጫና ውስጥ ይከተዋል።

በዚህም ባሕር በር የሌላቸው ሀገራት ቱሪስቶችን ለመሳብ በአየር መንገድ ላይ ብቻ ጥገኛ እንዲሆኑ ይገደዳሉ። ይህም የጉዞ ወጪን በከፍተኛ ሁኔታ ስለሚጨምረው፣ ቱሪስቶች አነስተኛ የወጪ አማራጭ ያላቸውን እና በየብስ ወይም በባሕር ትራንስፖርት በቀላሉ ሊደርሱባቸው የሚችሉ የባሕር ዳርቻ ሀገራትን ቀዳሚ ምርጫቸው እንዲያደርጉ እድል ይሰጣል።

የዓለም ቱሪስቶች በአንድ ጉዞ ውስጥ የተለያዩ ታሪኮችን፣ ባህሎችን፣ ተፈጥሮን እና መዝናኛ ስፍራዎችን አንድ ላይ ማግኘት ይፈልጋሉ።

የባሕር ዳርቻ መዳረሻ ያላቸው ሀገራት ታሪካዊ እና ባህላዊ ቅርሶቻቸውን ከባሕር ዳርቻ የውኃ ላይ ስፖርቶች እና ሪዞርቶች ጋር በማቀናጀት የተሟላ ፓኬጅ ማቅረብ ይችላሉ።

ይህ ዕድል ለኢትዮጵያ እና መሰል የባሕር በር ለሌላቸው ሀገራት አስቸጋሪ በመሆኑ፣ ቱሪስቶች በቆይታቸው ወቅት የሚጠብቁትን ሁለንተናዊ የዕረፍት ፍላጎት በአንድ ላይ ለማግኘት ይቸገራሉ።

የባሕር በር አለመኖር ታላላቅ የቱሪዝም ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ የሚያስችል ምቹ ሁኔታን አይፈጥርም። በዚህም በቱሪዝም ዘርፍ የሚጠበቀውን የውጭ ምንዛሪ እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ውስን እንዲሆን ያደርገዋል።

ምንም እንኳን ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በተመዘገቡ ታሪካዊ ቅርሶቿ፣ በደማቅ ባህሏ እና በዱር እንስሳት ሀብቷ በዓለም አቀፍ ደረጃ የምትታወቅ ቢሆንም፣ የባሕር በር መኖር ግን ለዘርፉ አዲስ እና ታሪካዊ ምዕራፍ ይከፍታል።

የባሕር በር ማግኘት ከታሪክ እና ከባህል ቱሪዝም ባሻገር፣ እስካሁን ያልተነካውን የባሕር ዳርቻ ቱሪዝም ለማልማት እና ዘመናዊ የባሕር ዳርቻ መዳረሻዎችን ለመፍጠር ሰፊ ዕድል ይሰጣል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድን ከባሕር በር መሠረተ-ልማት ጋር በማጣመር፣ ሀገራችን የአቪዬሽን እና የባሕር ቱሪዝምን ያቀናጀ የምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆንም ያስችላታል።

በመሆኑም የባሕር በር ጥያቄ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት እና ለሎጂስቲክስ መቃናት ብቻ ሳይሆን፣ የቱሪዝም ዘርፉን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሚወሰን ቁልፍ የስትራቴጂ አጀንዳ ነው።

በሃና ምንዳሁን