Search

ከትውልድ ባሻገር - ዛሬን ዘርተን ነገን ማጨድ

እሑድ ሰኔ 28, 2018 75

"የሚዘልቅ፤ የሚሻገር፤ የሚወረስ ነገር ስንሠራ በእኛ ዘመን እንኳን አትራፊ ባንሆን ልጆቻችን የአባቶቻቸውን ስም እያነሱ የሚያተርፉበት ሥራ ይሆናል፡፡" ይህ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ሰሞኑን ካስተላለፉት መልዕክት የተወሰደ ኃይለ ቃል ነው።

በዕለት ተዕለት ኑሯችን ውስጥ የምናከናውናቸው አብዛኞቹ ተግባራት የዛሬን ፍላጎት ለማርካት እና የዛሬን ችግር ለመቅረፍ የታለሙ ናቸው።

ሆኖም ግን የአንድን ሀገር ታሪክ የሚቀይሩ፣ የሕዝብን እጣ ፈንታ የሚያሻሽሉ እና በትውልድ መካከል ድልድይ የሚሆኑ ታላላቅ ሥራዎች የሚወለዱት ከዛሬ አልፎ ነገን ማየት ከሚችል አርቆ አሳቢ ዕይታ ብቻ ነው።

ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት የትርፍን ትርጉም ከግል እና ከጊዜያዊ ጥቅም አውጥቶ ወደ ትውልድ ቅርስ እና ዘላቂ ዐሻራ ከፍ የሚያደርግ ነው።

ዛሬ የምንገነባቸው መሠረተ ልማቶች፣ የምንተክላቸው ተቋማት እና የምናሳድጋቸው እሴቶች ሁሉ ነገን የሚወስኑ ናቸው።

የዛሬው ትውልድ መስዋዕትነት ክፍሎ ለነገው ትውልድ የደኅንነት፣ የብልጽግና እና የኩራት ምንጭ መሆን ይጠበቅበታል።

እውነተኛ ቅርስ ልጆቻችን እኛ በከፈልነው ዋጋ ላይ ቆመው አዲስ ሕይወት የሚገነቡበት መሠረት ነው።

ዛሬ የምናደርገው እያንዳንዱ አዎንታዊ ጥረት በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በትምህርት፣ በቴክኖሎጂ፣ በመሠረተ ልማት ግንባታም ይሁን በሰላም ግንባታ ነገ ልጆቻችን በዓለም አደባባይ አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲሄዱ እና "የአባቶቻችን ሥራ ነው" ብለው እንዲያተርፉበት ዕድል ይፈጥርላቸዋል።

አንዳንድ ሥራዎች ውጤታቸው ወዲያውኑ ላይታይ ይችላል። ልክ አንድ ትልቅ ዛፍ ተክሎ ጥላውን ሳያዩ እንደሚሄዱ አባቶች እኛም ዛሬ የምንለፋቸው ታላላቅ ሀገራዊ ሥራዎች ፍሬያቸው በቅቶ የሚበላው በትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ ሊሆን ይችላል።

ዋናው ቁምነገር ግን "እኛ ምን አተረፍንበት?" ሳይሆን "የሚወረስ ምን ነገር አስቀመጥን?" የሚለው ጥያቄን መመለስ ነው።

ይህ አስተሳሰብ ለሀገር መሪዎች ብቻ የተተወ ሳይሆን፣ እያንዳንዳችን በየተሰማራንበት የሙያ መስክ፣ በቤተሰባችን እና በማኅበረሰባችን ውስጥ "የሚዘልቅ ሥራ እየሠራሁ ነው?" ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል።

ዛሬ የምዘራው ዘር ነገ የሚጠበቅባትን ታላቋን ኢትዮጵያ ይሠራል። ለልጆቻችን ዕዳን ሳይሆን ዕድልን፣ እሮሮን ሳይሆን ታሪክን እናውርስ እንላለን።

በአድማሱ አራጋው