Search

የክልሎችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እና የተመጣጠነ ልማት ለማረጋገጥ እየተሠራ ነው - ፌዴሬሽን ምክር ቤት

እሑድ ሰኔ 28, 2018 97

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የድጎማ በጀት እና የጋራ ገቢዎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ 2018 በጀት ዓመት በክልሎች መካከል የተመጣጠነ ልማትን እና የዜጎችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በርካታ ውጤታማ ሥራዎች ማከናወኑን የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ሽመልስ አብዲሳ አስታወቁ።

አቶ ሽመልስ እንደገለጹት፣ ኮሚቴው የድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ክፍፍል ሥርዓት በጥናት እና በተደራጀ ዕቅድ እንዲመራ ተደርጓል፡፡

ወደ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚተላለፉ ሀብቶች ግልጽ እና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲከፋፈሉ የክትትልና የድጋፍ ሥራዎች መከናወኑን ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ ከተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት መካከል የሀብት ማከፋፈያ ቀመሮች በአግባቡ መተግበራቸውን መከታተል፣ ወደ ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች በሚተላለፉ ሀብቶች ላይ ግልጽነትን ማሳደግ፣ የበይነ-መንግሥታት የፊስካል ሽግግር ሥርዓትን ማጠናከር፣ የፌዴራል መሠረተ ልማት ስርጭት ፍትሐዊነትን ማስፈን እና ልዩ ዓላማ ያላቸው ድጎማዎች በግልጽነትና በተጠያቂነት ለክልሎች መከፋፈላቸውን ማረጋገጥ እንደሚገኙበት አመልክተዋል።

ሰብሳቢው አክለውም የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ዕድገትን ማፋጠን እንዲሁም በክልሎች መካከል ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን እውን ማድረግ የረጅም ጊዜ ጥረት የሚጠይቅ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ማነቆዎችን በመለየት እና መረጃዎችን በወቅቱ በማሰባሰብ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ኮሚቴው ሥራውን በትጋት እንደሚቀጥል አስረድተዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከተሰጡት ሥልጣን እና ኃላፊነቶች አንዱ በሀገራችን ውስጥ ፍትሐዊ የድጎማ እና የጋራ ገቢዎች ክፍፍል እንዲኖር ማድረግ መሆኑን ከፌዴሬሽን ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።