የዛሬ አሥራ አምስት ዓመት ገደማ በኢትዮጵያ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ የነበረው ትልቁ የቴክኖሎጂ ክርክር «ዌብሳይት ይኑራችሁ አይኑራችሁ» የሚል እና የነበሩትም ድረ-ገጾች መረጃ ቶሎ ቶሎ ተደራሽ የማያደርጉ ነበሩ።
ዛሬ ላይ ግን ኢትዮጵያ ከማዕድን፣ ከግብርና፣ ከኢንዱስትሪ እና ከቱሪዝም እኩል ቴክኖሎጂን አምስተኛው የሀገር ብልጽግና ምሰሶ አድርጋ በመቅረጽ ሥር ነቀል የዲጂታል ሽግግር እያደረገች ትገኛለች።
ባለፉት አምስት ዓመታት የታየው ይኸው ስትራቴጂካዊ ውሳኔ ቀደም ሲል እንደ ቅንጦት ይቆጠር የነበረውን የቴክኖሎጂ ምኞት ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚ መሰረተ ልማት ቀይሮታል።
ለዚህ ደግሞ ትልቁ ማሳያ የፌደራል እና የክልል ተቋማትን በአንድ የዲጂታል ሰንሰለት ያስተሳሰረው የመሶብ መተግበሪያ ነው።
መሶብ ልክ እንደ መንገድ እና አየር ማረፊያ ሁሉ ለሀገራችን የኢኮኖሚ መነቃቃት ቁልፍ መሰረተ ልማት ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ከ70 ቅርንጫፎች በላይ ተደራሽ ማድረግ የተቻለው ይህ ሥርዓት፣ ከማዕከል ወደ ባስ፣ ከዚያም ወደ ኤሌክትሪክ እና ጋዝ ተሽከርካሪዎች በመሸጋገር አሁን ላይ ወደ ዜጎች ተንቀሳቃሽ ስልክ መግባት ችሏል።
ይህ በአፍሪካ ደረጃ የመጀመሪያው የሆነ የተቀናጀ ሥርዓት ሲሆን ቴክኖሎጂ በከፍተኛ ፍጥነት እያንዳንዱን ዜጋ እንዴት ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚችል ያሳየ እውነታ ነው።
ከዚህ የቴክኖሎጂ ስኬት በስተጀርባ ያለው ትልቁ ኢኮኖሚያዊ ስሌት የጊዜ አጠቃቀምን የማዘመን ጉዳይ ነው። ሰዎች መለስተኛ አገልግሎቶችን ለማግኘት የሚያጠፏቸው ጊዜያት ሲደመሩ መንግሥታት በራሳቸው የአሠራር ድክመት ምክንያት ከዜጎች ሕይወት ላይ ዓመታትን ሊሰርቁ እንደሚችሉ ስንረዳ የዚህ መሰረተ ልማት ትርፍ ግልጽ ይሆናል።
ይህ የጊዜ ቁጠባ ዜጎች ተጨማሪ የኢኮኖሚ እሴት እንዲፈጥሩ እና ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ ትልቅ አቅም እየሆነ ነው። ከዚህ ባለፈም የቴክኖሎጂው ተፅዕኖ በከተማ ኮሪደር ልማት ላይ ከተገጠሙ የሲሲቲቪ ካሜራዎች ውጤታማነት ጀምሮ በቢሾፍቱ ኤርፖርት ግንባታ ላይ እስከሚንቀሳቀሱ እና በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) እስከሚታገዙ ግዙፍ የግንባታ ማሽነሪዎች ድረስ የጥራት ማረጋገጫ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
ማሽኖቹ ራሳቸው የአፈር ኮምፓክት ደረጃን እየለኩ የሚሰሩበት አሠራር ጊዜንና ገንዘብን ከመቆጠቡም በላይ፣ እንደ 3ዲ የቤት ግንባታ ቴክኖሎጂዎች ሁሉ የሀገራችንን የመሰረተ ልማት ጥራት ለትውልድ የሚሻገር የሚያደርግ ነው።
የዚህ ሁሉ የቴክኖሎጂ ስኬት የመጨረሻው ግብ ግን የዳታ እና የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ነው። የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እየገነባው ያለው ናሽናል ክላውድ በሀገራችን ያሉ ተቋማት ዳታ ሴንተሮች በጥምረት ያላቸውን አቅም በግማሽ የሚበልጥ ሲሆን የኢትዮጵያን መረጃ በምናውቀው ስፍራ ለማስቀመጥ እና እነማን እንደሚጠቀሙበት ለመቆጣጠር ታስቦ የተሰራ ነው።
ሉዓላዊነት ማለት ከዓለም መለየት ሳይሆን የእርስ በርስ መደጋገፉ በእውቀት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ማድረግ በመሆኑ ኢትዮጵያ ከሶፍትዌር ባለፈ የላፕቶፕ እና የአይፓድ ማምረቻ ፋብሪካዎችን ከኤአይ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን በመገንባት ላይ ትገኛለች።
ባለፉት አምስት ዓመታት 55 ሚሊዮን የቴሌብር ተጠቃሚዎች፣ ከ45 ሚሊዮን በላይ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ባለቤቶች እና 5 ሚሊዮን ኮደሮች ስልጠና እየተሰጠ መሆኑ ሀገራችን የደረሰችበትን የስኬት ከፍታ ያሳያል።
አሁን ላይ የመከላከያ ዘርፉ ድሮኖችን ማምረት እንደጀመረ ሁሉ መሶብን ጨምሮ ሌሎች የዲጂታል አገልግሎቶችም የሀገር ውስጥ ፍላጎትን አሟልተው ወደ ውጭ ሀገራት በመላክ የውጭ ምንዛሬ የሚያመጡበት እና ወደ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የሚስፋፉበት አዲስ ምዕራፍ ተጀምሯል።
በበረከት ሽመልስ