Search

“በትግራይ ክልል ህጻናትን ጨምሮ ሰላማዊ ዜጎች በግዳጅ እየተመለመሉ ነው” ፦ ሂውማን ራይትስ ዎች

ሰኞ ሰኔ 29, 2018 54

በትግራይ ክልል ህገ-ወጡ የህወሓት ቡድን እድሜያቸው 15 ዓመት የሆኑ ታዳጊዎችን ጨምሮ ሰላማዊ ዜጎችን በማፈን በግዳጅ ወደ ጦርነት እየመለመሉ መሆኑን ሂውማን ራይትስ ዎች ዛሬ ባወጣው አዲስ ሪፖርት አጋልጧል።

ይህ ሕገ-ወጥ የግዳጅ ምልመላ ዘመቻ በመላው ክልሉ ከፍተኛ የፍርሃት ድባብን መፍጠሩንም ነው ተቋሙ ያስታወቀው።

እንደ ሂውማን ራይትስ ዎች መግለጫ፣ ከሚያዝያ 2026 . ጀምሮ የትግራይ ኃይሎች እና ህገ-ወጡ የህወሓት ቡድን የቀድሞ ተዋጊዎችን፣ ወንዶችን እና ታዳጊዎችን በመንገድ ላይ፣ በቢሮዎች፣ በምሽት የቤት ለቤት ፍተሻዎች፣ እንዲሁም ለወጣቶች ዋነኛ የሥራ ዕድል ከሚፈጥሩ የወርቅ ማዕድን ማውጫ ሥፍራዎች ሳይቀር እያፈኑ ይገኛሉ።

የድርጅቱ የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ዳይሬክተር ሌቲሺያ ባደር፣ ባለስልጣናቱ ይህንን ዘመቻ በአስቸኳይ አቁመው በሕገ-ወጥ መንገድ የመለመሏቸውን ዜጎች ወደ ቤተሰቦቻቸው ሊመልሱ ይገባል ብለዋል።

ምንም እንኳን ህገ-ወጡ የህወሓት ቡድን ይህንን የግዳጅ ምልመላ ክስ በማስተባበል ዜጎች ክልሉን ለመከላከል በፈቃዳቸው እየተቀላቀሉ ነው ቢሉም፣ የዓይን እማኞች እና የቤተሰብ አባላት ግን አፈናው መጠነ ሰፊና አስገዳጅ መሆኑን ይመሰክራሉ።

ለምሳሌ በዓዲ ጉደም ከተማ የባጃጅ አሽከርካሪዎች፣ የውኃ ሻጮች፣ የቀን ሠራተኞች እና አርሶ አደሮች ሳይቀሩ በመንገድ ላይ እየታፈኑ መወሰዳቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ከዚህም አልፎ ወጣቶች ከምልመላው ለማምለጥ አካባቢያቸውን ለቀው ሲሰደዱ፣ ባለስልጣናቱ የታዳጊዎቹን ቤተሰቦች (እናቶችን ጨምሮ) በማሰር እና በማንገላታት ቤተሰብ ላይ የጅምላ ቅጣት እየፈጸሙ መሆኑን ሪፖርቱ በስፋት አብራርቷል።

ተቋሙ ባወጣው መግለጫ፤ ይህ የግዳጅ ምልመላ ድርጊት 1949ኙን የጄኔቫ ስምምነትን የሚጥስ እና በተለይም 15 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎችን በጦርነት ውስጥ ማሳተፍ የጦር ወንጀል መሆኑን አሳስቧል።

በመሆኑም የአፍሪካ ኅብረትን ጨምሮ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት የሚደግፉ እንደ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ ኬንያ እና ደቡብ አፍሪካ ያሉ ሀገራት፤ የትግራይ ባለስልጣናት ይህንን የግዳጅ ምልመላ በአስቸኳይ እንዲያቆሙ እና የታፈኑ ሕጻናትንም እንዲለቁ ጠንካራ ጫና ሊያደርጉ እንደሚገባ ሂውማን ራይትስ ዎች ጥሪውን አቅርቧል።