በአንድ ሀገር ሁለንተናዊ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ሽግግር ውስጥ የፀጥታና ደህንነት ተቋማት ያላቸው ሚና የሀገረ መንግስቱ የጀርባ አጥንትነት ነው። በኢትዮጵያ የዘመናዊ ፖለቲካ ታሪክ ውስጥ፣ እነዚህ ተቋማት ከሀገርና ከህዝብ ዘላቂ ደህንነት ይልቅ ለገዢዎች ፖለቲካዊ ፍላጎት ማስፈፀሚያነት ሲያገለግሉ የቆዩበት ዘመን እጅግ ረጅም ነበር።
የተቋማቱ ፖለቲካዊ ወገንተኝነትና በዜጎች ላይ የነበራቸው አፋኝ ባህሪ ጥልቅ የተቋም ስብራት ፈጥሮ ቆይቷል። ሆኖም ከ2010 ዓ.ም. ወዲህ የተተገበረው ጥልቅ ሪፎርም ይህንን መዋቅራዊ ብልሽት በመጠገን፣ የፀጥታ ዘርፉን ወደ እውነተኛ ሀገራዊ የቁመና ከፍታ አሸጋግሮታል።
የሪፎርሙ መሰረታዊ እሳቤ የመነጨው "መደመር" ከተሰኘው ሀገር በቀል ፍልስፍና ሲሆን፣ ማጠንጠኛው ተቋማቱን ሀገር አስቀጣይና በህዝብ ዘንድ አመኔታን ያተረፉ ተቋማት ማድረግ ነው። የለውጡ ፍልስፍናዊ መሰረት በአምስት ምሰሶዎች ላይ የቆመ ነው። ከፖለቲካ ወገንተኝነት ማላቀቅ፣ ዴሞክራሲያዊና ተጠያቂነት ያለው አሰራር መዘርጋት፣ የብዝሃነት ውክልናን ማረጋገጥ፣ ቴክኖሎጂያዊ ልዕልናን መጎናፀፍ፣ እንዲሁም ማኅበረሰብ-ተኮር መሆን ናቸው።
ይህ ውስብስብ ሪፎርም የተመራው ደፋር በሆነ የከፍተኛ አመራር ለውጥ፣ የሲቪል ተጠያቂነትን ባረጋገጠ መዋቅራዊ ሽግግር እና አፋኝ ህጎችን በማሻሻል ነው። በዚህም ተቋማቱ ከፖለቲካ መሳርያነት ወደ እውነተኛ ፕሮፌሽናል የመረጃና ፀጥታ ተቋምነት የተሸጋገረበት የለውጡ ማዕከላዊ ማሳያ ነው።
የሪፎርሙ ትልቁ ትሩፋት ቁልፍ የፀጥታ ተቋማት በተግባር ያስመዘገቡት ታሪካዊ ስኬት ነው፡፡ ለአብነት ለማንሳት ያህል፡-
የሀገር መከላከያ ሠራዊት፡ ቴክኖሎጂና ትጥቅ ከውጭ በማስገባት ላይ የነበረውን ጥገኝነት በመስበር፣ ዘመናዊ ድሮኖችን እስከ ማምረት የደረሰ የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነትን አረጋግጧል። በተጨማሪም ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ፈርሶ የነበረውን የባህር ሀይል ዳግም በማቋቋም በቀይ ባህር ቀጠና የኢትዮጵያን ጂኦፖለቲካዊ ተፅዕኖ ለማሳደግ በተጠንቀቅ ላይ ይገኛል፡፡
ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት (NISS)፡ ተቋሙ ከነበረበት አስከፊ ስያሜና ተቋማዊ ሁኔታ በመውጣት የሀገርን ሉዓላዊነት ወደ ማስጠበቅ የሚያስችል ጥልቅ እና የተደራጀ የልህቀት ደረጃ አድጓል። በመረጃ ትንተናና በቴክኖሎጂ አጠቃቀሙ እጅግ እያደገ በመምጣት በምሳሌነት በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ የተቃጡትን ጨምሮ በርካታ ውስብስብ ብሔራዊና ዓለም አቀፋዊ ስጋቶችን በቅድመ-መረጃ በማክሸፍ አስተማማኝ የመረጃ ትንተና አቅሙን በተጨባጭ አሳይቷል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (INSA)፡ የዲጂታል ሉዓላዊነት ዘብ በመሆን፣ በኢትዮጵያ ቁልፍ መሰረተ ልማቶች ላይ የተሰነዘሩ በርካታ የሳይበር ጥቃቶችን በተሳካ ሁኔታ ያመከነ ሲሆን፣ የፐብሊክ ኪ ኢንፍራስትራክቸር (PKI) የህዝብ ቁልፍ መሰረተ ልማት በማስጀመር የዲጂታል ዳታ ልውውጥ ደህንነትን በአስተማማኝ መሰረት ላይ አኑሯል።
የፌደራል ፖሊስ፡ በ2013 ዓ.ም በፀደቀው አዲስ ዶክትሪን መሰረት፣ ፖሊስን ከወታደራዊ ባህሪ በማላቀቅና ማህበረሰብን ያሳተፈ የቅድመ-መከላከል (SARA ሞዴል) አሰራርን ተግባራዊ በማድረግ፣ ከሪፎርም በፊት አጥቶት የነበረውን የህዝብ አመኔታ ዳግም እየገነባውና አስተማማኝ የሰላም ዘብነቱን በተግባር አረጋግጧል፡፡
በእነዚህ ተቋማት የታየው የድልና የስኬት ሚስጥር "የህግ የበላይነት"፣ "የቴክኖሎጂ ልዕልና" እና "የአካታችነት" ስትራቴጂካዊ ውህደት ነው። ሪፎርሙ ያመጣው መሰረታዊ ለውጥ፣ ተቋማቱ ከስርዓት ደህንነት ጠባቂነት (Regime Security) ወደ ዜጋ ደህንነት አገልጋይነት (Human Security) ያደረጉት ፅንሰ-ሀሳባዊ ሽግግር ነው። ከማፈን ወደ ቅድመ-መከላከል፣ ከማስፈራራት ወደ ማህበረሰባዊ ትስስር፣ እንዲሁም ከውጭ ጥገኝነት ወደ ሀገር በቀል የቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ መሸጋገራቸው የስኬቱ ሚስጥር ነው። ብዝሃነትን ያረጋገጠው አመራርም ተቋማቱ በህዝብ ዘንድ ያላቸውን ቅቡልነት (Legitimacy) በእጅጉ አሳድጎታል።
በአጠቃላይ፣ የኢትዮጵያ የፀጥታና ደህንነት ተቋማት ሪፎርም በኢትዮጵያ ከተከናወኑት መዋቅራዊ ለውጦች እጅግ ስኬታማውና የኢትዮጵያ ኩራት ነው ብንል ማጋነን አይሆንም። ምንም እንኳን ከውስጥ ግጭቶችና ከጂኦፖለቲካዊ ጫናዎች ጋር ተያይዘው የመጡ ፈታኝ ሀገራዊ ስጋቶች ቢያጋጥሙም፣ ተቋማቱ በከፍተኛ ጽናት ሀገራዊ ሉዓላዊነትን አስጠብቀዋል። በብቃትም ተሻግሯል፡፡ ሪፎርሙ የፖለቲካ ታማኝነትን ሰብሮ ህገ-መንግስታዊ ታማኝነትን በማፅናቱ ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልፅግና ጠንካራ መሰረት ጥሏል። ቀጣዩ ሀገራዊ ኃላፊነት ይህንን ተቋማዊ ጥንካሬ ይበልጥ በማጎልበት፣ የተጀመረውን የሽግግር ፍትህ ሂደት ስኬታማ በማድረግ የዘላቂ ሰላምና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታውን ዳር ማድረስ ይሆናል።
በአዶኒያስ ወ/አረጋይ