32ኛውን የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP32) ለማስተናገድ ሰፊ ዝግጅት እያደረገች የምትገኘው ኢትዮጵያ፤ ከቀደምት አዘጋጅ ሀገራት ልምድና ተሞክሮ የመቅሰም ሥራዋን በከፍተኛ ሁኔታ አጠናክራ ቀጥላለች።
በዚሁ መሠረት፣ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የኮፕ 32 ፕሬዚዳንት ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በብራዚል ከCOP 30 ፕሬዝዳንት አምባሳደር አንድሬ አራንሃ ኮሪያ ዶ ላጎ እና ከልዑካን ቡድናቸው ጋር ፍሬያማ የሁለትዮሽ ውይይት አካሂደዋል።
የውይይቱ ዋና ዓላማ ይህንን ታላቅና ዓለም አቀፋዊ የአየር ንብረት ጉባኤ በስኬት ከመምራትና ከማዘጋጀት ጋር የተያያዙ ስልታዊ ዕውቀቶችን፣ የአሠራር ጥበቦችን እና ጠቃሚ የተወሰዱ ትምህርቶችን በስፋት ለመለዋወጥ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
በውይይቱም ብራዚል ግዙፉን የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባኤ በስኬት ለመምራት የተገበረቻቸውን ስትራቴጂዎችና ያካበተችውን ተሞክሮ ለኢትዮጵያ አቻዋ አጋርታለች።
ይህ የልምድ ልውውጥ ኢትዮጵያ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው መሪዎች፣ ተደራዳሪዎችና የዓለም ሕዝብ የሚሳተፉበትን ይህንን ታሪካዊ ጉባኤ በላቀ ብቃትና ስኬት ለማዘጋጀት ለምታደርገው ጥረት አጋዥ እንደሚሆንም ተመላክቷል።
በአዝመራው ሞሴ