የሀገር ዘላቂ ብልጽግና ዕውን ሊሆን የሚችለው የዜጎችን ፍትሐዊና እኩል ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ አርቆ አሳቢ ፖሊሲዎች ተቀርጸው ወደ ተግባር ሲቀየሩ ብቻ ነው፡፡
የከተማና የገጠር ትስስር ደግሞ የሀገር ዕድገት ሚዛኑን ጠብቆ፣ ሁሉንም ዜጋ እኩል ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ ታላቅ ሚና አለው፡፡
ኢትዮጵያ ያሏትን የተፈጥሮና የሰው ኃይል ጸጋዎች ለሕዝቧ ሁለንተናዊ ጥቅም ለማዋል ሌት ተቀን እየሠራ የሚገኘው የመደመር መንግሥት፣ ይህንን ሚዛናዊ እሳቤ መሠረት በማድረግ ፍቱን ፖሊሲዎችን ቀርጾ በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል፡፡
ከእነዚህም መካከል የከተማና ገጠር ልማት ትስስር ፖሊሲ ግንባር ቀደሙና ዋነኛው ማሳያ ነው፡፡
ነባሩ ፖሊሲ እና በከተሞች ላይ የነበረው የተዛባ አተያይ
ቀደም ሲል የነበሩ የልማት ፖሊሲዎች፣ በተለይም ግብርና መር የኢንዱስትሪ ልማት (ADLI) ስትራቴጂ ከተማን እና ገጠርን ባልተመጣጠነ እና በፖለቲካዊ ክፍፍል ላይ በተመሠረተ እይታ ይቃኙ ነበር፡፡
በነባሩ ሥርዓት ውስጥ "የምንቆመው ለአርሶ አደሩ ነው" የሚል መሪ ቃል በስፋት ይስተጋባል፡፡ ከተማን ግን "የትምክህተኞች እና አፈንጋጭ ምሁራን መሰብሰቢያ" አድርጎ የመፈረጅ ግትር ርዕዮተ-ዓለማዊ አዝማሚያ ተንሰራፍቶ ነበር፡፡
ይህ ዓይነቱ ዋልታ የረገጠ ክፍፍል በከተሞች እና በገጠር መካከል ያለውን ተፈጥሯዊ እና ምጣኔ-ሀብታዊ ትስስር አዳክሞት ቆይቷል፡፡
በዚህም ምክንያት ከተሞች እሴት የሚጨምሩ የኮኖሚ ማዕከላት እንዳይሆኑ፤ ይልቁንም ከውጭ የሚገቡ ሸቀጦች ማራገፊያ ብቻ ሆነው እንዲቆዩ አድርጓቸዋል፡፡
አዲሱ የከተማ ልማት ፖሊሲና የ"ስሉጥ ከተማ" ራዕይ
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ የሆነው የመደመር ፍልስፍና ይህንን መዋቅራዊ ስብራት በአዲስ እሳቤ ለመጠገን በስፋት እየሠራ ይገኛል፡፡
አዲሱ ፖሊሲ ከተማን በተዛባ መንገድ ከማየት ወጥቶ "ስሉጥ ከተማ" (Smart City) የመገንባት ራዕይን ያነገበ ነው፡፡
ስሉጥ ከተማ ማለት መንግሥትን፣ የግል ዘርፉን፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን እና ማኅበረሰቡን በማስተባበር ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረገ ዘላቂ ብልጽግናን የሚያረጋግጥ ማዕከል ነው፡፡
አዲሱ ፖሊሲ "የሌማት ትሩፋት" የተሰኘውን ሀገራዊ መርሐ-ግብር ከከተማ ግብርና ጋር በማስተሳሰር በከተማ ፕላን ውስጥ አካትቷል፡፡
ይህ ስትራቴጂ በከተሞች ውስጥ ያሉ ክፍት ቦታዎችን በመጠቀም አትክልት እና ፍራፍሬ፣ እንዲሁም የእንስሳትና የዶሮ እርባታን በስፋት ማልማትን ያካትታል፡፡
ይህም የከተማ ነዋሪዎችን የምግብ ወጪ ከ10 እስከ 20 በመቶ በመቀነስ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚረዳ ነው፡፡ አሁንም ለበርካታ ሴቶችና ወጣቶችም ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ላይ ይገኛል፡፡
የገጠር መሬት አዋጅና የፋይናንስ መዋቅራዊ ለውጥ
ሚዛናዊ ልማትን ለማምጣት ከተወሰዱት ታላላቅና ታሪካዊ እርምጃዎች አንዱ አዲሱ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 1324/2016 ነው፡፡
ይህ አዲስ አዋጅ የገጠር መሬት ይዞታ መብትን ለባንክ ብድር ዋስትና አድርጎ ለመጠቀም የሚያስችል ጠንካራ ሕጋዊ መሠረት ጥሏል፡፡
በዚህም መሠረት አርሶ አደሩ የፋይናንስ አቅርቦት በቀላሉ እንዲያገኝ በማድረግ ግብርናውን ከበሬ ትከሻ ወደ ዘመናዊ ሜካናይዜሽን ለማሸጋገር ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፡፡
ይህ ፖሊሲ አርሶ አደሩን የዘመናዊ ኢኮኖሚው ቀጥተኛ ተዋናይ እና ተጠቃሚ ያደርገዋል፡፡
የኮሪደር ልማት፡ የከተማና ገጠር ትስስር ማሳያ
በቅርቡ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች እየተተገበረ የሚገኛው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት፣ የመደመር እሳቤን በተግባር ያረጋገጠ ሌላኛው ሀገራዊ የሪፎርም ፍሬ ነው፡፡
የከተማ ኮሪደር የነዋሪዎችን የመኖሪያና የሥራ አካባቢ ደረጃ ሲያሻሽል፤ የገጠር ኮሪደር ልማት ደግሞ ገቢን ማሳደግ ብቻ ሳይሆን አርሶ አደሩ ባህሉንና ወጉን ጠብቆ ንጹሕና ውብ አካባቢን እንዲፈጥር፣ አኗኗሩን እንዲያሻሽልና ዘመናዊ መሠረተ ልማቶችን እንዲጠቀም እያስቻለ ነው፡፡
የገጠር ኮሪደሩ አርሶ አደሩ በግቢው ውስጥ ትራክተርና መኪና የሚያቆምበትን ዘመናዊ አኗኗር የሚፈጥር ነው፡፡ መንገዶቹ ደግሞ አርሶ አደሩ ምርቱን በፍጥነትና በቅናሽ ዋጋ ወደ ከተማ ገበያ እንዲያቀርብ በማድረግ ምቹ የገበያ ትስስር ይፈጥራል፡፡
ይህ የከተማና የገጠር ትስስር በዚህ ብቻ የሚያበቃ አይደለም፡፡ መንግሥት ከ"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ስትራቴጂ ጋር በማቀናጀት አርሶ አደሩንና የከተማውን ነጋዴ በቀጥታ በመረጃ ቴክኖሎጂ ለማስተሳሰር እየሠራ ይገኛል፡፡
በተጨማሪም ሀገራዊ የግብርና ምርት ኤክስፖርትን ለማሳደግ በገጠር የሚመረቱ የኢንዱስትሪ ግብዓቶች በከተማ አካባቢ ባሉ የአግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርኮች እሴት ተጨምሮባቸው ወደ ውጭ ገበያ እንዲቀረቡ እየተደረገ ይገኛል፡፡
በዚህም አዲሱ የመደመር የልማት ፍልስፍና ለዘመናት የዘለቀውንና ዋልታ የረገጠውን ሰው ሠራሽ ክፍፍል በጽኑ መሠረቱ በመስበር፤ ከተማና ገጠር እጅና ጓንት ሆነው ለሀገር የጋራ ብልጽግና የሚተጉበትን ወርቃማና ዘመናዊ መንገድ ከፍቷል፡፡
እነዚህ አርቆ አሳቢ ፖሊሲዎችና አዋጆች የሁላችንንም የነገ ብሩህ ተስፋ ሰንቀው የተነሱ፣ በተግባርም ተጨባጭና ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን እያስመዘገቡ ያሉ የለውጥ ፍሬዎች ናቸው፡፡
በመንግሥትና በሕዝብ የጋራ ጥረት ከተሞቻችን ለኑሮ ምቹና ሳቢ፤ ገጠሮቻችን ደግሞ የዘመናዊ ግብርና እና የብልጽግና ማዕከል እንዲሆኑ እየተሠራ ነው፡፡
በዚህ ታሪካዊና ሀገራዊ የለውጥ ጉዞ ውስጥ የሁሉም ዜጋ ንቁና ገንቢ ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ፣ ሁሉም እጅ ለእጅ ተያይዞ ብሩህቷን ኢትዮጵያን በጋራ ማልማት ለነገ የማይባል የቤት ሥራ ነው፡፡
በለሚ ታደሰ
#Ethiopia #EBC #SmartCity #UrbanAndRuralDevelopment #Medemer #Prosperity #CorridorDevelopment