Search

በድሬዳዋ በ3.6 ቢሊዮን ብር ወጪ የ17 ኪሎ ሜትር ዘመናዊ መንገዶች ተገንብተዋል፡- ከንቲባ ከድር ጁሃር

ሰኞ ሰኔ 29, 2018 48

የድሬዳዋ አስተዳደር በ2018 በጀት ዓመት በከተማ ማደስና ማስዋብ ዘርፍ ከ3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ 17 ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ ዘመናዊ መንገዶችን መገንባቱን ከንቲባ ከድር ጁሃር አስታወቁ።

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት 3ኛ የሥራ ዘመን፣ 5ኛ ዓመት፣ 12ኛ መደበኛ ጉባዔውን ዛሬ ማካሄድ ጀምሯል።

የአስተዳደሩን የአስፈፃሚና የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት ያቀረቡት ከንቲባ ከድር ጁሃር፤ በዓመቱ የነዋሪዎችን መሠረታዊ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ ሰፋፊ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

እንደ ከንቲባው ገለጻ፣ በከተማ ማደስና ማስዋብ ዘርፍ በተከናወኑ ተግባራት 17 ኪሎ ሜትር ዘመናዊ መንገዶች የተገነቡ ሲሆን፣ ለዚህም ከ3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጓል።

ግንባታው የከተማዋን የንግድ እንቅስቃሴ ከማሳደጉም ባለፈ፣ ለ10 ሺህ ዜጎች አዲስ የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ በትግበራ ላይ ከነበሩት የካፒታል ፕሮጀክቶች መካከል 94ቱ ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ክፍት መሆናቸውን ጠቁመዋል ከንቲባ ከድር ጁሃር።

ከንቲባው በአስተዳደሩ 51 የሰንበት ገበያዎችን በማቋቋም አምራቾችን እና ሸማቾችን በቀጥታ ማገናኘት ተችሏል ብለዋል። ይህም የዋጋ ንረትን ከ28 በመቶ ወደ 13 ነጥብ 4 በመቶ ዝቅ እንዲል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጸዋል።

የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን ለማቀላጠፍና የተገልጋዮችን እርካታ ለመጨመር "ድሬ መሶብ" በተሰኘው የአንድ ማዕከል አገልግሎት አማካኝነት ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል።

ምክር ቤቱ ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚህ ጉባዔ፣ በቀረበው ሪፖርት ላይ ተወያይቶ ከማጽደቁም ባለፈ፣ የ2019 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት ላይ መክሮ ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

በቴዎድሮስ ታደሰ