Search

የአንጋፋዋ ድምፃዊት ራሔል ዮሐንስ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ

ሰኞ ሰኔ 29, 2018 85

በኢትዮጵያ የባህል ሙዚቃ ታሪክ ውስጥ የማይረሳ አሻራ ያሳረፈችው የአንጋፋዋ ድምፃዊት ራሔል ዮሐንስ ሥርዓተ ቀብር፤ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች፣ ወዳጅ ዘመዶቿና በርካታ የሙያ አድናቂዎቿ በተገኙበት በዛሬው ዕለት በደብረ ምጥማቅ ሰዓሊተ ምሕረት ቤተክርስቲያን ተፈፅሟል።

ድምፃዊት ራሔል ዮሐንስ በተለየ የድምፅ ቀለምና በባህል ዜማዎቿ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትን ያተረፈች ሲሆን፣ በኪነ-ጥበብ ዘመኗ 13 የሙዚቃ አልበሞችን ለሕዝብ አበርክታለች።

ከዚህም ባለፈ ከተለያዩ ዕውቅ ድምፃውያን ጋር በመጣመር በርካታ ዘመን አይሽሬና ተወዳጅ ሥራዎችን ለአድማጮች አድርሳለች።

ከያኒዋ ካበረከተቻቸው በርካታ የሙዚቃ ሥራዎቿ መካከል "ኢትዮጵያ"፣ "አራዳ"፣ "እንደ ኢየሩሳሌም"፣ "ትዝታ"፣ "አንቺ ባለድሪ" እና "አየር ኃይላችን" የሚሉት ተጠቃሽ ሲሆኑ፣ እነዚህ ዜማዎች ዛሬም ድረስ በሕዝብ ልብ ውስጥ የታተሙና ተወዳጅነታቸው የማይደበዝዝ ድንቅ የጥበብ ሥራዎቿ ናቸው።

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ለአንጋፋዋ አርቲስት ራሔል ዮሐንስ ቤተሰቦች፣ የጥበብ ባልደረቦችና ለመላው አድናቂዎቿ መጽናናትን ይመኛል።