Search

የአምራች ኢንዱስትሪው ብሔራዊ የሀብት ልየታ ጥናት ተጠናቅቆ ወደ ትግበራ ተሸጋገረ

ሰኞ ሰኔ 29, 2018 52

ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲከናወን የቆየው የአምራች ኢንዱስትሪው ብሔራዊ የሀብት ልየታ ጥናት መጠናቀቁን ተከትሎ፣ የትግበራ ማስጀመሪያ መድረክ ዛሬ ተካሂዷል።

በሀገር ውስጥ እና በውጭ አገር በሚኖሩ የዘርፉ ከፍተኛ ምሁራን የተሳተፉበት ይህ ጥናት፣ የኢትዮጵያን የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በአዲስ መልክ ለማነቃቃት ያለመ ነው።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል፣ የሀገራት ልዕልና እና ዕድገት በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በሚደረግ መዋቅራዊ ለውጥ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ገልጸዋል።

ቀደም ሲል ለዘርፉ ይሰጥ የነበረው ትኩረት ውስን እንደነበረ ያስታወሱት ሚኒስትሩ፣ አሁን ላይ ግን መንግሥት በወሰዳቸው የፖሊሲ ማሻሻያዎች ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ ሰፊ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ተጨባጭ ውጤቶች እያስመዘገቡ መሆናቸውን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ በዘርፉ የተደረጉ የፖሊሲ ማስተካከያዎች የውጭ ንግድን በማሳደግ፣ ኢንቨስትመንትን በማበረታታት እና በ"ኢትዮጵያ ታምርት" ብሔራዊ ንቅናቄ አማካኝነት አበረታች ውጤቶች መገኘታቸውን አብራርተዋል።

የጥናቱ ዋና ዓላማ በየአካባቢው እና በየክልሉ የሚገኘውን ሀብት በመለየት፣ ቀልጣፋና ፍትሃዊ የኢንቨስትመንት ሥርዓት መፍጠር እንዲሁም የሀብት ስምሪትን ውጤታማ ማድረግ ነው።

በጥናቱ የተሰበሰበው መረጃ በዲጂታል መንገድ ተደራሽ የሚደረግ ሲሆን፣ ይህም ለባለሀብቶችና ለሚመለከታቸው አካላት ግልጽ እና ምቹ የሆነ አሠራር ለመፍጠር እንደሚያስችል ተገልጿል።

በመድረኩ የክልል ርዕሰ መስተዳደሮች፣ ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

በሂሩት እምቢአለ