የዓለማችን የኢኮኖሚ ትርክት እና የአሸናፊነት ምስጢር በከፍተኛ ፍጥነት እየተቀየረ ነው። የዓለም የአእምሮአዊ ንብረት ድርጅት (WIPO) እና የብሪክስ የጥናት ተቋማት በቅርቡ ይፋ ያደረጉት ዓለም አቀፋዊ ትንተና እንደሚያረጋግጠው፣ የዓለም ኢኮኖሚ ከተፈጥሮ ሀብት ጥገኝነት በመላቀቅ ዕውቀትንና የሰውን ልጅ አእምሮአዊ ፈጠራ መሠረት ወዳደረገ መዋቅራዊ ሽግግር ገብቷል።
በዚህ አዲስ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ፉክክር ማዕበል ውስጥ ሀገራችን ኢትዮጵያ ዳር ሆና አልተመለከተችም። እስከ 2030 የሚዘልቀውን ሀገራዊ የ“ዲጂታል ኢትዮጵያ” ስትራቴጂን መሠረት በማድረግ፣ ስትራቴጂያዊ የጅማሮ ሞዴልን (Strategic Start Model) በተጨባጭ እና በውጤታማነት እየተገበረች ትገኛለች።
የጥናቱ ማብራሪያ በግልጽ እንደሚያስቀምጠው፣ የወደፊቱ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ የበላይነትና የገበያ ተወዳዳሪነት የሚወሰነው በመሬት ውስጥ ባለው የተፈጥሮ ሀብት ክምችት ሳይሆን፤ አዲስ ዕውቀትን የመፍጠር፣ የአእምሮአዊ ንብረትን የመጠበቅና የመመዝገብ፣ እንዲሁም የፈጠራ ውጤቶችን ወደ ገበያ ምርትነት የመቀየር አቅም ላይ ነው።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ሰፊ የሆነውን ወጣትና አምራች የሰው ኃይሏን ከዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጋር በማስተሳሰር፣ ወደ ከፍተኛ የዕውቀት ማማ ለመሸጋገር የሚያስችላትን ጠንካራ ስትራቴጂካዊ መሠረት እየገነባች ነው።
በተለይም በብሪክስ ጥምረት ውስጥ እንደ ቻይና እና ሕንድ ያሉ አገራት በሳይንስና ምርምር ኢንቨስትመንት እንዲሁም በመረጃ ቴክኖሎጂ (IT) አገልግሎት ኤክስፖርት እያስመዘገቡት ያለውን ከፍተኛ ዓለም አቀፋዊ እምርታ መመልከት ይቻላል።
ሀገራችንም ይህንን የስኬታማ ፈለግ በመከተል የዲጂታል ክፍያ ሥነ-ምህዳሯን በከፍተኛ ፍጥነት እያስፋፍች ትገኛለች።
ይህ የጀመርነው የዲጂታል ጉዞ፣ በቀጣዮቹ ጥቂት ዓመታት የሰው ሀብታችንን ወደ ብቁ አምራች የዕውቀት ኃይል በመቀየር ከአዲሱ ዓለም አቀፍ የዕውቀት ኢኮኖሚ ቀጥተኛ ተጠቃሚ እንድንሆን በእጅጉ የሚያግዘን መሆኑን ሪፖርቱ ጠቁሟል።
የነገዋ ኢትዮጵያ በዕውቀት፣ በቴክኖሎጂ እና በዲጂታል ፈጠራ ላይ የተገነባች ጠንካራ ሀገር ትሆናለች።
በሰለሞን ገዳ