Search

የ5ቱ ዓመታት ገፆች፤ ታሪክ ተሰርቷል!

ሰኞ ሰኔ 29, 2018 46

የዘመናት ታሪክ ገፆች ሲገለጡ  የአንድ ሀገር ዕጣ ፈንታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከስር መሰረቱ ተነቅንቆ አዲስ መልክ የሚይዝበት አጋጣሚ እጅግ ጥቂት ነው።

ላለፉት አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ የተዘረጉትን የልማትና የለውጥ ገፆች ስናነብ፣ የተካሄደው ጉዞ "ለውጥ" ወይም "ሪፎርም" በሚሉ ቃላት ብቻ የሚገለፅ አይደለም።

ይልቁንም ከሪፎርም ባሻገር ወደ አብዮት የተጠጋ፣ የኢትዮጵያን አጠቃላይ ገፅታ የለወጠና ሥር ነቀል መዋቅራዊ ሽግግርን ያረጋገጠ ታላቅ ብሔራዊ ንቅናቄ ነው።

በዓለም የኢኮኖሚ ታሪክ ውስጥ፣ ጥቂት ሀገራት ብቻ ናቸው በፈጣን ጊዜ ውስጥ አስደናቂ የሚባል የዕድገት ዝላይ (Leapfrogging) ማሳየት የቻሉት።

ቻይና በሰላሳ ዓመታት ያመጣችው መዋቅራዊ ለውጥ፣ ደቡብ ኮሪያ በጄኔራል ፓርክ ቹንግ ሂ ቆራጥ መሪነት የተጓዘችው የኢንዱስትሪ ሽግግር፣ እንዲሁም ታይዋን ያስመዘገበችው የቴክኖሎጂ ስኬት ሁሌም በምሳሌነት ይነሳሉ።

ነገር ግን፣ ኢትዮጵያ በአምስት ዓመታት ውስጥ ብቻ እያስመዘገበች ያለው የለውጥ ፍጥነትና ስፋት እጅግ አስደናቂ ሆኖ እናገኘዋለን። በጠንካራና ቁርጠኛ አመራር እየተመራች፣ ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ  ወደ ታላቅነት የምታደርገው ሽግግር ከግምት በላይ የሆነ ጉዞ ነው።

ይህ ተአምራዊ የሚባል ዝላይ በገሃድ ከሚታይባቸው መስኮች አንዱ ግብርና ነው። ለዘመናት በልመናና በስንዴ ዕርዳታ ጥገኝነት ስትታወቅ የነበረችው ሀገር፣ በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ የምግብ ሉዓላዊነቷን አረጋግጣ ወደ ስንዴ ላኪነት መሸጋገሯ እውነተኛ የኢኮኖሚ "ሉዓላዊነት" ማረጋገጫ ነው።

በተጠናከረ የኩታገጠም እና የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት፣ የስንዴ ምርት በ2017 በጀት ዓመት 280 ሚሊዮን ኩንታል መድረሱ የዚህ ፈጣን ስኬት ማሳያ ነው። ኢኮኖሚው ከአንድ ወጥ ጥገኝነት ወጥቶ ወደ ብዝሃ-ዘርፍ ልማት በማደግ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገቡ በጥቂት ሀገራት ብቻ የሚሳካ ታላቅ ድል ነው።

የለውጡ ጅረት በግብርና ብቻ አልተገታም። በአረንጓዴ ኢኮኖሚው ዘርፍ፣ እስከ ኮፕ ጉባኤ ድረስ ከ65 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል በእስካሁኑ ጉዞ የሀገራችንን የደን ሽፋን ከ17 በመቶ ወደ 23.6 በመቶ ከፍ በማድረግ ኢትዮጵያ የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ መከላከያ ተምሳሌት ሆናለች።

በውሃና ኃይል (ኤነርጂ) ሽግግር፣ ታላቁን የሕዳሴ ግድብን ጨምሮ በርካታ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ የኃይል ማመንጨት አቅምን ወደ 9,554 ሜጋ ዋት አሳድጋለች።

በተለይም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን (EV) በመጠቀም የነዳጅ ጥገኝነትን መቀነስና የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ሌላው የዘርፉ ስኬት ነው።

በከተማ ልማት ዘርፍም የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች ከተሞቻችንን የውበት፣ የንፅህናና የሥልጣኔ ማዕከል አድርገዋቸዋል።

በኢንዱስትሪና በዲጂታል ዘርፍ፣ "ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄንና የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን በመተግበር፣ እንዲሁም ከ58 ሚሊዮን በላይ የቴሌብር ተጠቃሚዎችን በማፍራትና የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ቁጥር በማስፋፋት ዘመኑን የዋጀ የቴክኖሎጂ አብዮት ተካሂዷል።

በማዕድን ዘርፍ የተከናወኑት የሪፎርም ስራዎችም እንዲሁ እጅግ አስደናቂ ናቸው። የኮንትሮባንድ ንግድን በመግታትና የወርቅ ምርትን ከ3.3 ቶን ወደ 38.8 ቶን በማሳደግ፣ ዘርፉ የውጭ ምንዛሬ ግኝታችንን ወደ ላቀ ደረጃ አሸጋግሯል።

የቱሪዝም ዘርፉም በተመሳሳይ በገበታ ለሀገርና በሌሎች የቱሪዝም መዳረሻዎች ልማት፣ የውጭ ቱሪስት ፍሰትን ወደ 1.3 ሚሊዮን በማድረስ ሀገራችንን ወደ ተፈጥሯዊ የቱሪዝም መዳረሻነት ቀይሯታል።

በዲፕሎማሲውና በፖለቲካው መስክም የተመዘገበው ስኬት የሚያስደምም ነው። ኢትዮጵያ የነበሩባትን ውስብስብ ጫናዎች በብልሃት ተቋቁማ፣ የውጭ ፖሊሲዋን ሚዛናዊ በማድረግ ወደ ብሪክስ (BRICS) አባልነት መቀላቀሏ ዓለም አቀፍ ተደማጭነቷን አረጋግጧል።

በድምሩ ሲታይ እነዚህ ሁሉ ስኬቶች በአንድ ላይ ሲገመገሙ ኢትዮጵያ በእርግጥም ተአምራዊ በሚባል የለውጥ ጎዳና ላይ ትገኛለች። ይህን ሁሉ ውስብስብ ሀገራዊ፣ ቀጠናዊና ዓለም አቀፍ ጫና ተቋቁሞ ማሳካት የቻለው "መፍጠር፣ መፍጠንና መዝለል" በሚል መርህ የተቃኘው የፖለቲካ ኢኮኖሚ ሥርዓትና ቆራጥ አመራር በመኖሩ ነው።

ይህ እንደ አዲስ የጀመረው የለውጥና የዝላይ ጉዞ በአጭር ጊዜ ከግብ ሲደርስ፣ ኢትዮጵያ በብልፅግና ማማ ላይ ደምቃ በመውጣት የአፍሪካዊ ተምሳሌትነትን አልፋ የዓለም የብልፅግና ተምሳሌት እንደምትሆን አያጠራጥርም።

የ5ቱ ዓመታት ገፆች፣ የዚህችን ታላቅ ሀገር አይበገሬነትና ትንሣኤ በደማቁ የፃፉ ህያው የድል ድርሳናት ናቸው!

በአዶኒያስ ወ/አረጋይ