Search

እውን "ቶዮታ" በውሃ ኃይል ብቻ የሚሰራ መኪና ይፋ አድርጓል?

ዓርብ ነሐሴ 09, 2017 86

ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያ ላይ "ቶዮታ" ያለ ባትሪ ወይም ቻርጅ በውሃ ሀይል ብቻ የሚንቀሳቀስ መኪና ይፋ አድርጓል የሚል ሀሰተኛ መረጃ ይዞ ወጥቷል።

"የዓለማችን ትልቁ የመኪና አምራች የሆነው ቶዮታ በዓይነቱ ልዩ የሆነ እና ውሃን እንደ ኃይል ምንጭነት የሚጠቀም መኪና ይፋ አድርጓል" የሚል ሲሆን በሰበር ዜና መልክ ተለቅቆ ሚሊዮኖች ጋር የደረሰ መረጃ ነው።

ቶዮታ ለቀቀ የተባለው አዲሱ ቴክኖሎጂ ታዲያ የሊቲየም ባትሪዎችን ወይም የነዳጅ ጣቢያዎችን አገልግሎት እንደሚያስቀር መረጃው ያትታል።

 



በተጨማሪም የተሰራጨው መረጃ ቻይና ከእንግዲህ በኤሌክትሪክ መኪናዎች ያላትን ተወዳዳሪነት ልታጣ እንደምትችል በመጠቆም የተሻለ ተአማኒነት ለማግኘትም የቻይናውን ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ምስል አካትቷል።

ነገር ግን "ቶዮታ" ለኤ.ኤፍ.ፒ ፋክት ቼክ እንዳረጋገጠው ኩባንያው "የውሃ ሞተር" ተብሎ ሊገለጽ የሚችል ምንም አይነት ቴክኖሎጂ እያዘጋጀ አይደለም።

የውሃ ኃይል አንድ ቀን ነዳጅን ሊተካ ይችላል የሚለው ተስፋ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እያበበ ያለ አዲስ ሀሳብ ቢሆንም ይህ መላ ምት በጠንካራ ሳይንሳዊ ማስረጃዎች የተደገፈ አይደለም ሲል ኤ.ኤፍ.ፒ ፋክት ቼክ ገልጿል።

በመሆኑም "ቶዮታ" በውሃ የሚሰራ ሞተር ይፋ አድርጓል የሚለው መረጃ የተሳሳተ መሆኑ ተረጋግጧል።

#etv #ebc #ebcdotstream #FactCheck #fakenews #Cybersecurity