Search

"የትግራይ ወጣቶች ከእናት እቅፍ በጉልበት እየተቀሙ ነው" – በክልሉ እየተካሄደ ያለው የግዳጅ ምልመላ ሕዝቡን እያማረረ ይገኛል

ረቡዕ ሐምሌ 01, 2018 210

በትግራይ ክልል ውስጥ የሚፈጸመው የወጣቶች አፈሳ እና የግዳጅ ምልመላ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመምጣቱ፣ የክልሉ ተወላጆች በምሬት አቤቱታቸውን እያሰሙ ነው።

ከኢቲቪ ትግርኛ ጋር ቆይታ ያደረጉ ወጣቶች እንደገለጹት፣ የህወሓት ህገ ወጥ ቡድን የትግራይን ወጣቶች ከእናት እቅፍ በኃይል እየቀማ ወደ ማሰልጠኛ ካምፖች በማገት ሰቆቃቸውን እያባባሰ ይገኛል።

እነዚህ ለለውጥ ዝግጁ ያልሆኑ አካላት፣ ወጣቶቹን ምንም ዓይነት ዓላማ ለሌለው የፖለቲካ ትርፍ መጠቀሚያ እያደረጓቸው እንደሆነ ወጣቶቹ በቁጭት ተናግረዋል።

የቡድኑ የኮሚኒኬሽን እና የጽህፈት ቤት ኃላፊዎች በክልሉ ምንም ዓይነት የወጣቶች አፈሳ እንደሌለ በይፋ ቢናገሩም፣ ወጣቶቹ ይህንኑ ንግግር "ሕዝብን መሸወድ" ሲሉ አውግዘውታል።

ቡድኑ ለትግራይ ሕዝብ ምንም ዓይነት አዘኔታ እንደሌለው ያረጋገጠው ይህ ድርጊት፣ ወጣቶች በገዛ ሀገራቸው ተረጋግተው እንዳይኖሩ በማድረጉ፣ በርካታ ወጣቶች ወደ ሰላማዊው ኢትዮጵያ ክፍል ለመሰደድ እየተገደዱ መሆኑንም ገልጸዋል።

ጽንፈኛው ቡድን የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት በመጣስ፣ ክልሉን ዳግም ወደ ጦርነት አዘቅት ለመክተት ቀን ከሌሊት እየሠራ መሆኑንም ወጣቶቹ አጋልጠዋል።

በተለይም "ፅምዶ" በሚል ስያሜ የጀመሩት አፍራሽ አካሄድ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በማበር የትግራይን ሕዝብ ወደማይወጣው የጥፋት አዘቅት የሚገፋ አደገኛ ድርጊት መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

በስተመጨረሻም መላው የትግራይ ማኅበረሰብ፣ የህወሓት ጽንፈኛ ቡድን እየተከተለ ያለው መርህ አልባና አጥፊ አካሄድ በጋራ ሊያወግዘው እና "በቃችሁ" ሊለው እንደሚገባ ወጣቶቹ በአጽንኦት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በጎሳዬ /ኪዳን

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: