Search

ከምርጫ ማሸነፍ ማግስት የሚደረጉ የእንግዳ አቀባበልና የድግስ ሥነ ሥርዓቶች ጊዜን የሚያባክኑ በመሆናቸው ሊቀሩ ይገባል፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ረቡዕ ሐምሌ 01, 2018 112

ከምርጫ ማሸነፍ ማግስት የሚደረጉ የእንግዳ አቀባበልና የድግስ ሥነ ሥርዓቶች ጊዜን የሚያባክኑ በመሆናቸው ሊቀሩ እንደሚገባና በቀጥታ ወደ ሥራ መግባት እንደሚያስፈልግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ገልፀዋል።

ጉዳዩ ምንም እንኳ ለምክር ቤቱ ብቻ ጠቃሚ ባይሆንም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ግልጽ መሆን ስላለበት ያነሱት መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከድግስ ይልቅ በቀጥታ ወደ ሥራ መግባት እንደሚቀድም አስገንዝበዋል።

ባለፈው በተደረገው ምርጫ ፓርቲያቸው ማሸነፉን አስታውሰው በወቅቱ በነበረው ዓለም አቀፋዊ የፖለቲካ አውድ መሠረት ባለሥልጣናትንና እንግዶችን በመጋበዝ የክብር ሥነ ሥርዓት ማከናወናቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይሁን እንጂ ወደፊት እንዲህ ዓይነቱን አካሄድ አስፈላጊ ነው ብለው እንደማያምኑና ሂደቱ "ጊዜን ማባከን" መሆኑን ተናግረዋል።

ሕዝቡ በምርጫ ወቅት "ሥራ ስሩልን" ብሎ መምረጡን በማንሳትም፣ ፓርላማው የሚመርጠውን አካል ከመረጠ በኋላ ወዲያውኑ ወደ ሥራ መግባት እንጂ እንግዳ ሲቀበሉና ሲሸኙ ጊዜ ማባከን አስፈላጊ እንዳልሆነ አብራርተዋል።

በጉዳዩ ላይ ጥያቄ ላላቸው አካላት ግልጽ መልስ ለመስጠት እንደሚፈልጉ በመግለጽም፣ ወደፊት በሚኖሩ አጋጣሚዎች ሁሉ "የሚጋበዝም ሆነ የሚደገስ የለም፣ ሥራ ይቀጥላል" በማለት ቁርጠኛ አቋማቸውን አስታውቀዋል።

የዚህ ዓይነቱ ሥነ ሥርዓት በዓለም አቀፍ ደረጃም ያለውን ተግዳሮት ሲያስረዱም፤ በተለያዩ ሀገራት ለሚደረጉ መሰል ሁነቶች መሄድና አለመገኘት ራሱን የቻለ ችግር መሆኑንና ተጠርቶ በሚቀርበት ወቅት የቅሬታ ስሜት እንደሚፈጥር ገልጸው፣ በሂደቱም ጋባዡም ሆነ ተጋባዡ ሲቸገሩ መታዘባቸውን ጠቁመዋል።

በመጨረሻም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰው ለማስተናገድና ነገሮችን ለማስተካከል ከሚባክነው ጊዜ ይልቅ በሀገር ውስጥ ባህል ቀለል ባለው መስተንግዶ ላይ ማተኮር እንደሚገባ አሳስበዋል።

በብሌን ደምበሎ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: