Search

አሸናፊ ሁሉንም ይወስዳል ፖለቲካ ማክተምና አዲሱ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ምዕራፍ

ረቡዕ ሐምሌ 01, 2018 128

የመደመር ፍልስፍና በፅንሰ-ሀሳብ ደረጃ ሶስት ዋና ዋና ምሰሶዎች አሉት እነሱም የነበሩ መልካም እሴቶችን ጠብቆ ማቆየት የጎደሉትን መሙላት እና የታሪካዊና ትርክት ስብራቶችን በአዲስ ሀገራዊ ስምምነት መጠገን ናቸው።

ይህ ፍልስፍና ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ የተሞከሩትን እና ፍፁም ተቃራኒ የነበሩትን ፖለቲካዊ ፅንፎች ማለትም ያለፈውን ታሪክ ሙሉ በሙሉ የሚያቆሽሸውን አፍራሽ ትርክት እና የነበረውን ስርአት ያለምንም ለውጥ ለማስቀጠል የሚሞክረውን ግትር አካሄድ የሚያስታርቅ ሦስተኛ አማራጭ ሆኖ ቀርቧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመደመርን ዋና ግብን ሲያብራሩ "የመደመር ፍልስፍና ዋና ዓላማ ባለፉት ዘመናት የነበሩ እቅዶችን ማረቅ፣ የተሰበሩትን መጠገንና የጎደሉትን በመሙላት የጋራ ብልጽግናን ማረጋገጥ ነው" በማለት ይገልጹታል።

በዚህም መሠረት በፖለቲካዊ ሽኩቻ የደቀቀችውን ሀገር በጋረ ትርክትና በተግባር በማከም ወደ ጋራ ብልጽግና ማምራት የተቻለ ሲሆን ባለፉት አምስት ዓመታት የተመዘገቡት የፖለቲካና የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ስኬቶች የዚሁ እሳቤ ቀጥተኛ ነጸብራቅ ናቸው።

የመደመር ፍልስፍና በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ላይ ያመጣው ትልቁ ለውጥ የ"አሸናፊ ሁሉንም ይወስዳል" የፖለቲካ ባህልን መስበሩ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ማብራሪያቸው ወቅት ገዥው ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ምህዳሩን ለማስፋት ሲል ከመቶ በመቶ መቀመጫዎች ውስጥ በሰማንያ አምስት በመቶው ላይ ብቻ ለመወዳደር መወሰኑና ቀሪውን አስራ አምስት በመቶ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች በነጻነት መተው በአፍሪካ የምርጫ ታሪክ እጅግ ያልተለመደና አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ተግባር መሆኑን በጥብቅ አሳይተዋል።

ይህ የሚያሳየው ስልጣንን ለብቻ የመጠቅለል አባዜን በመስበር፣ የተወካዮች ምክር ቤት የብዙሃን ድምጽ እና የተለያዩ ፖለቲካዊ አመለካከቶች ማስተናገጃ እንዲሆን የተደረገውን ጥረት ነው።

ውሳኔው በምርጫ ማሸነፍን ብቻ ሳይሆን ከምርጫ በኋላ ያለውን የሀገር ግንባታ ሂደት ያማከለ በመሆኑ ቀደም ሲል በጠላትነት ይተያዩ የነበሩ ተፎካካሪ ፖለቲከኞች በመንግስት መዋቅር ውስጥ፣ በከፍተኛ የሚኒስትርነት እና የአመራር ቦታዎች ላይ ተካተው እንዲሰሩ መንገድ ፈጥሯል።

ይህን አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ፖለቲካን ከጥፋትና ከሕልውና ትግል ወደ አማራጭ ሐሳብ ማምጫ ማማ ከፍ አድርገነዋል" በማለት ገልጸውታል።

ከተለመደው የስልጣን ማራዘም አባዜ በተለየ መልኩ ብልጽግና ፓርቲ የሚመራዉ መንግስት ከፍተኛው የስልጣን ዘመን በሁለት ዙር እንዲገደብ ፍላጎቱ መሆኑ ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መሰረት ይጥላል ተብሎ ይታመናል።

ይህ ሀሳብ በኢትዮጵያ ታሪክ ዘላቂ የፖለቲካ አለመረጋጋት ምንጭ የሆነውን የስልጣን ማራዘም አባዜን በህግ የሚገታ በመሆኑ፣ የወደፊቱን የሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ባህል ዋስትና የሚሰጥም ነው።

በታሪካዊው ምርጫ ወቅት የታየው የህዝብ ተሳትፎ የመደመር ፍልስፍና ከላይ ወደ ታች የሚወርድ ብቻ ሳይሆን ከታች ወደ ላይ በህዝብ ፍላጎት የሚደገፍ መሆኑን አሳይቷል።

ህዝቡ በተለያዩ አካባቢዎች የነበሩ የጥይት ድምጾችን፣ የጸጥታ ስጋቶችንና ማስፈራሪያዎችን ወደ ጎን በመተው በነቂስ ወጥቶ መርጧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይህንን ታሪካዊ ወቅት በፓርላማ ሲያስታውሱ "የኢትዮጵያ ሕዝብ በማስፈራሪያና ዛቻ ሳይገታ፣ በነቂስ ወጥቶ በመምረጥ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና ለሀገረ መንግሥት ጽናት ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር አሳይቷል" ብለዋል።

ይህ ሂደት ህዝቡ ለመንግስት የሰጠው ባዶ ቼክ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፤ ይህም ማለት ህዝቡ ለሰላም፣ ለሀገራዊ ጽናት እና ለአንድነት ያለውን ጥማት በተግባር ያሳየበት ነው።

በተመሳሳይ ጊዜ ጽንፈኝነትን፣ ታሪካዊ የሀገር ክህደት አዝማሚያዎችን እና ዘረኝነትን በአንድ ድምጽ የኮነነበት የህዝብ ብስለት መገለጫ ሆኖ አልፏል።

ከዚሁ የፖለቲካ ብስለት ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋትን በዘላቂነት ለመፍጠር የተከናወኑት ተግባራት የመደመርን አቀራረብ ግልጽ አድርገው ያሳያሉ።

የመደመር ፍልስፍና ሰላምን የሚተረጉመው በጠመንጃ ሃይል የመጣ ጸጥታን ብቻ ሳይሆን ውስጣዊ መግባባትንና የማህበረሰብ ትስስርን ጭምር ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምክር ቤት ማብራሪያቸው "እውነተኛ ሰላም የሚረጋገጠው በጠመንጃ ኃይል ሳይሆን በውይይትና በሕዝባዊ ምክክር ነው" በማለት ደጋግመው አጽንኦት ሰጥተዋል።

በዚህም መሠረት ባለፉት ዓመታት የተካሄዱት ከሁለት መቶ ሃያ አምስት በላይ ከህዝብ ጋር የተደረጉ ቀጥተኛ ውይይቶችና በየደረጃው የተፈጠሩት ከአራት ሺህ በላይ መድረኮች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።

በእነዚህ ሰፊ የምክክር ሂደቶች ምክንያት ቀደም ሲል የነበሩ የማህበረሰብና የሃይማኖት ግጭቶች እንዲቀንሱ ተደርጓል። በተለይም በጦርነትና በግጭት ውስጥ የነበሩ የታጠቁ ኃይሎችን በሰላማዊ መንገድና በድርድር ለመመለስ የተደረገው ጥረት፣ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነትን ጨምሮ፣ ሀገርን ከማጽናት ባለፈ አሸናፊና ተሸናፊ ሳይኖር እኩል ተቀምጦ የመወያየት ባህልን አምጥቷል።

ፍልስፍናው አሸናፊና ተሸናፊ የሌለበትን ሁለቱም ወገኖች ተቀምጠው በመወያየት ለሀገር ሰላም የሚበጀውን የሚመርጡበትን አዲስ የድርድር ባህል በተግባር አሳይቷል።

መንግስት ለሰላም ሲል በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ማድረጉ፣ ከስልሳ ሺህ በላይ የታጠቁ ኃይሎችን መልሶ ማቋቋሙና የተያዙ ሀብቶችንና ንብረቶችን ሳይነኩ መመለሱ ለሀገራዊ አንድነት የተከፈለ ትልቅ ዋጋ እና የወንድማማችነትን ስሜት ለመመለስ የተደረገ ተግባራዊ እርምጃ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይህንን ከባድ የሰላም ዋጋ ሲያብራሩ "ለሀገራዊ አንድነትና ለወንድማማችነት ስንል የከፈልነው ዋጋ የሰላምን ዘላቂነት ከማረጋገጥ የመነጨ የፖለቲካ ብስለት መገለጫ ነው" በማለት ገልጸውታል።

ይህ የሰላም አማራጭ እንዳለ ሆኖ ሀገርን የማጽናት ስራው ያለ ጠንካራ መከላከያ እንደማይሳካ በመገንዘብ የጸጥታ ተቋማትን በቁጥር፣ በብቃትና በቴክኖሎጂ በማዘመን ሀገርን ከማንኛውም ጥቃት የመከላከል አቅም ተፈጥሯል።

ይህ ማሻሻያ ኢትዮጵያን ከውስጥም ሆነ ከውጭ ሊሰነዘሩባት የሚችሉትን ማናቸውንም ጥቃቶች የመከላከል እና ሉዓላዊነቷን የማስከበር ብቃት ፈጥሮላታል።

ባጠቃላይ የመደመር ፍልስፍና በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከፅንሰ-ሀሳብ ባለፈ ወደ ተግባራዊ ፖሊሲና እርምጃዎች መተርጎሙን ያሳያል።

ፍልስፍናው ባለፉት ዓመታት የታዩትን ታሪካዊ ስብራቶች ለመጠገን፣ በምርጫ ሒደት ውስጥ አካታችነትን ለማስፈን እና በጦርነት ውስጥ የነበሩ ኃይሎችን ወደ ሰላማዊ ማዕቀፍ ለማምጣት እንደ ትልቅ የፖለቲካ ኮምፓስ ሆኖ አገልግሏል።

ይህ ጉዞ ተግዳሮቶች ቢኖሩበትም ለዘላቂ ዲሞክራሲ እና ለጋራ ብልጽግና የተጣለ ጠንካራ መሰረት መሆኑን ማሳያ ነው።

በበረከት ሽመልስ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: