Search

የአፍሪካ የሕክምና ተቋማት ኮንፈረንስ ለኢትዮጵያ የጤና ፖሊሲ ትልቅ ግብዓትና ተጨባጭ ውጤት የተገኘበት ነው፡- የጤና ሚኒስቴር

ረቡዕ ሐምሌ 01, 2018 118

በኢትዮጵያ አዘጋጅነት ሲካሄድ የቆየው የአፍሪካ የሕክምና ተቋማት ኮንፈረንስ (Mededafrica 2026) ዛሬ ሦስተኛ ቀኑን የያዘ ማጠቃለያ መርሃ ግብሩን እያከናወነ ነው።

በማጠቃለያው መርሐ ግብር ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሳረላ አብዱላሂ እንደገለጹት፤ በኮንፈረንሱ በተካሄዱት ውይይቶች ኢትዮጵያ ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ጠቃሚ መረጃዎችን ያገኘችበት ብሎም የራሷን ተሞክሮ ለሌሎች ሀገራት ያካፈለችበት መድረክ ሆኗል።

የጤና እና የትምህርት ዘርፍ ሥራዎች የሚያስመዘግቧቸውን ውጤቶች ወዲያውኑ ለማወቅ አስቸጋሪ ቢያደርጋቸውም፣ በሂደት ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ከዘርፉ ተዋናዮች ጋር የሚደረጉ ውይይቶች ወሳኝ መሆናቸውን ሚኒስትር ዴኤታዋ አብራርተዋል።

በጉባኤው ላይ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ የጤናው ዘርፍ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ ሲሆን፣ በዘርፉ ላይ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮችና መፍትሔዎቻቸውን በተመለከተ የልምድ ልውውጥ አድርገዋል።

ይህንን መሰል ኮንፈረንሶች ኢትዮጵያ ታላላቅ አህጉራዊ ጉባኤዎችን ለማስተናገድ ያላትን ልምድ ይበልጥ የሚያዳብሩ መሆናቸውም ተገልጿል።

በዚሁ መርሃ ግብር ማጠቃለያ ላይ በዘርፉ ጉልህ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የጤናው ዘርፍ መምህራን፣ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት የእውቅናና የምስጋና ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል።

የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች በአዲስ አበባ እየተከናወኑ የሚገኙ የኮሪደር ልማት ሥራዎችን እንደሚጎበኙም ይጠበቃል።

በመሃሪ ዓለሙ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: