Search

ቁጥሮች ይናገራሉ፡- ዓመታት ይታዘባሉ

ረቡዕ ሐምሌ 01, 2018 141

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የዘመናት ውዝፍ ስራዎችንና የባከኑ ታሪካዊ እድሎችን በሚያካክስ መልኩ እጅግ አስደናቂና ግዙፍ የኢኮኖሚ ስኬቶችን እያስመዘገበች ትገኛለች።

ለዘመናት ሀገራችን የተጓዘችው የኤሊ ጉዞ በድህነት አዙሪት ውስጥ እንድትቀር አድርጓት ቆይቷል። ሆኖም፣ የመደመር መንግሥት ይህንን የተደራረበ የኋላ ቀርነት ችግር ለመቅረፍና የባከነውን ጊዜ ለማካካስ፣ የተለመደውን አዝጋሚ ጉዞ በመተው "የዝላይ ስትራቴጂን" (Leapfrogging)፣ የፈጠራ (Innovation) እና የፍጥነት (Speed) መንገድን አጥብቆ መከተል እንዳለበት ያምናል።

ይህን የፍጥነትና የፈጠራ እሳቤ በተግባር በማረጋገጥ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ማብራሪያ መሰረት፣ ሀገራችን አሁን ላይ የ17፣ የ27 ዓመታት እና ከዚያም በላይ የሆኑ የትናንት ታሪኮችን በአንድ አመት ገደማ ያጠቃለለችበት የብልጽግና ምዕራፍ ላይ በኩራት ደርሳለች ብለዋል።

የ17 ዓመታት ስኬት በአንድ ዓመት መቋጨት በውጭ ንግድ (ኤክስፖርት) ዘርፍ ኢትዮጵያ ዘንድሮ 11 ቢሊዮን ዶላር ገቢ በማስገኘት ሀገራዊ ታሪክን የቀየረ ግዙፍ ክንውን አስመዝግባለች።

ይህ አሃዝ ዝም ብሎ ስሌት ሳይሆን፣ ከ1984 እስከ 2000 ዓ.ም ባሉት 17 ተከታታይ ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ ካገኘችው አጠቃላይ የኤክስፖርት ገቢ ጋር እኩል የሆነ ነው።

በተለይም የኢትዮጵያ አንጡራ ሀብት በሆነው በቡና ኤክስፖርት ዘርፍ፣ ኢትዮጵያ ለ17 ዓመታት ወደ ውጭ ልካ ያገኘችው አጠቃላይ የዶላር መጠን 3.3 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ሲሆን፣ ዘንድሮ በአንድ አመት ውስጥ ብቻ 3.1 ቢሊዮን ዶላር በማግኘት የ17 ዓመቱን አዝጋሚ ጉዞ በአንድ አመት የፍጥነት ዝላይ ማሳካት ችላለች።

ይህ እመርታዊ ለውጥ (Nonlinear growth) የተገኘው ዘመናትን የፈጀውን የደረጃ በደረጃ ጉዞ በመዝለል፣ አዳዲስ አሰራሮችን በማፍለቅና አቅምን አሟጦ በመጠቀም ነው።

የ27 ዓመታት ውጤት በአንድ ዓመት ሲገለጥ በማዕድን ዘርፍ በተለይም የወርቅ ኤክስፖርትን ስንመለከት ውጤቱ ይበልጥ አስደማሚና የፈጠራን ሃያልነት የሚያሳይ ሆኖ እናገኘዋለን።

ከ1984 እስከ 2011 ዓ.ም ባሉት 27 የውድቀትና የመከራ ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የላከችው አጠቃላይ የወርቅ መጠን 3.7 ቢሊዮን ዶላር ብቻ የነበረ ሲሆን፣ ዘንድሮ በአንድ አመት ገደማ ብቻ ወደ 5.5 ቢሊዮን ዶላር በማግኘት የ27 ዓመቱን ታሪክ በአንድ አመት መብለጥ መቻሏ የዝላይ ስትራቴጂን ተግባራዊነት ያረጋግጣል።

በሀገር ውስጥ ገቢ አሰባሰብም የኢኮኖሚ አሻጋሪነት ራዕይ ደምቆ ይታያል። በ27 ዓመታት ውስጥ የተሰበሰበው አጠቃላይ ገቢ 1 ትሪሊዮን ብር ገደማ የነበረ ሲሆን፣ ዛሬ ዘመናዊ አሰራርንና ፈጠራን በማቀናጀት ዘንድሮ በአንድ አመት ከ1.5 ትሪሊዮን ብር በላይ ገቢ በማስገባት የ27 ዓመቱን ጥረት 150 በመቶ በአንድ አመት መሰብሰብ ተችሏል።

ይህ የሚያሳየው፣ የመደመር መንግሥት ተስፈንጥሮ ከፍታ ላይ ለመድረስ ያለውን ስነ-ልቦናዊና የተግባር ዝግጁነት ነው።

ከ20 እጥፍ በላይ ያደገው አቅም እና የማይበገር ማክሮ ኢኮኖሚ ከእነዚህ የዘመናት ስኬቶችን ወደ አንድ አመት ካመቁ ውጤቶች ባሻገር፣ ኢትዮጵያ ራሷን ከድንገተኛ አለም አቀፍ ንዝረቶች የምትጠብቅበት የውጭ ምንዛሬ ክምችቷ (Reserve) ከጥቂት አመታት በፊት ከነበረው አቅም ከ20 እጥፍ በላይ በማደግ ኢትዮጵያ አለም አቀፍ የኢኮኖሚ ጫናዎችን የመቋቋም አቅሟን አፈርጥማለች።

ይበልጥ አስገራሚው ደግሞ፣ መንግሥት ይህንን ሁሉ ስኬት ያመጣው የሀገርን ሉዓላዊነትና የነገ ትውልድ ነጻነትን አደጋ ላይ ከሚጥል እዳ በመራቅ፣ ላለፉት 8 ዓመታት አንድም ዶላር የንግድ ብድር (Commercial Loan) ሳይበደር መሆኑ ውጤቱን ይበልጥ ታሪካዊና ስትራቴጂካዊ ያደርገዋል።

በዚህም የተጠናና የተናበበ ሁሉን አቀፍ ጥረት፣ አጠቃላይ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከ10.2 እስከ 10.3 በመቶ ያድጋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ይህም በአፍሪካ ትልቁ ዕድገት ሆኖ በኩራት ተመዝግቧል።

በአጠቃላይ፣ እነዚህ አስደማሚ ቁጥሮች እና ድንቅ ስኬቶች ኢትዮጵያ የመደመር መንግሥት በሚከተለው የ"ፍጥነት፣ ፈጠራ እና ዝላይ" አስተሳሰብ የዘመናትን የተከማቸ የድህነት እዳ በአጭር ጊዜ ማካካስ እንደምትችል በተግባር ያረጋገጡበት ግዙፍ ማሳያ ናቸው።

የብዙ አስርት አመታትን ስራ በአንድ አመት በማጠናቀቅ፣  "ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ" ከሆነው የድህነት አዙሪት በሀይል ተፈንጥራ ወጥታለች።

ቁጥሮቹ የሚመሰክሩት ይህንን እውነት ነው፤ ኢትዮጵያ ወደ ተጨባጭ ብልጽግና የምታደርገው ጉዞ ወደማይቀለበስበት ምዕራፍ መሸጋገሩን የዘመናችን ታሪክና አመታት በትዝብትና በአድናቆት እያዩት ይገኛሉ።

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: