የወቅቱ የግብፅ የማወናበጃ ፕሮፓጋንዳ
ሰሞኑን የግብፅ ሚዲያዎች ከወትሮው የተለየ እና የተቀነባበረ የማወናበጃ ፕሮፓጋንዳ ጀምረዋል፡፡ ይህ ዘመቻ ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መሠረት ያደረገ ቢመስልም፣ ጉዳዩ ከዚያም ያለፈ የረጅም ጊዜ ሤራ ያዘለ ነው፡፡
በተለይም ኢትዮጵያ ምርጫዋን በሰላም አጠናቅቃ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር ልጆቿን ሰብስባ እየመከረች ባለችበት በአሁኑ ወቅት ይህ ወከባ መጀመሩ በአጋጣሚ የተፈጠረ አይደለም፡፡
የግብፅ ሚዲያዎች በሕዳሴው ግድብ ላይ ብቻ ሳይሆን ከረጅም መጓተት በኋላ ሥራው ተጀምሮ ሌሊት እና ቀን እየተገነባ ባለው የመገጭ ግድብ ላይ ጭምር መዝመታቸው በልዩ ትኩረት ሊታይ የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡
ስለሆነም፣ ኢትዮጵያውያን መረጃን መሠረት በማድረግ ለብሔራዊ ጥቅማቸው ዘብ እንዲቆሙ፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ግብፅ ከጥንት ጀምሮ በኢትዮጵያ ላይ ስትከተል የኖረችውን የከሰረ የፖለቲካ ሤራ በተከታታይ ይተነትናል፡፡
የሤራው ታሪካዊ ዳራ
ዛሬ ላይ ሆነን ስናየው ግብፅ በኢትዮጵያ ላይ የምትከተለው የፕሮፓጋንዳ እና የማወክ ፖሊሲ የቅርብ ጊዜ ክስተት ሊመስለን ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህ ሤራ ሥረ-መሠረቱ እጅግ የጠለቀ ታሪካዊ መሰረት ያለው ነው፡፡
ኢትዮጵያን የመበጥበጥ እና የማፍረስ ሤራ በግብፅ የፖለቲካ መዝገብ ውስጥ ግንባር ቀደሙን ስፍራ ይይዛል፡፡ ይህን እውነት ግብፅ ቀጥተኛ ወታደራዊ ወረራ እስከመፈጸም የደረሰችበትን የ19ኛውን ክፍለ ዘመን የታሪክ ምዕራፍ መለስ ብለን ስንቃኝ ፍንትው ብሎ ይታየናል፡፡
በ19ኛው ክፍለ ዘመን ኬዲቭ እስማኤል የተባለው የግብፅ መሪ የጥንቷን ግብፅ የገናናነት ዘመን ለመመለስ በማሰብ፣ ወደ ሱዳን፣ ኢትዮጵያ እና የሶማሊያ የባሕር ዳርቻዎች ግዛቱን የማስፋፋት ሕልም ነበረው፡፡
ይህንኑ ሕልሙን ለማሳካትም በ1857 ዓ.ም ምፅዋን ከኦቶማን ቱርክ በመረከብ ቨርነር ሙንዚንገር የተባለውን ስዊዘርላንዳዊ ጀብደኛ እና ቅጥረኛ የምፅዋ አስተዳዳሪ አድርጎ ሾመው፡፡
ይህ እርምጃ ኢትዮጵያን በኃይል ለመውረር ካልተቻለም ደግሞ እርስ በእርስ አጋጭቶ በማዳከም የዘለዓለም የትርምስ ቀጣና ለማድረግ የተወጠነ "የሙንዚንገር ዶክትሪን" አካል ነበር፡፡
የማጋጨት እና የመከፋፈል ስትራቴጂ
ግብፅ ይህንን የሤራ ድር ለመሸረብ የተጠቀመችው ዋነኛ ስልት የኢትዮጵያን የውስጥ ክፍፍል ማራገብ ነበር፡፡ በወቅቱ ኢትዮጵያን ይመሩ የነበሩትን አፄ ዮሐንስ አራተኛን ለመውጋት የሸዋውን ንጉሥ ምኒልክን ማስታጠቅ እና አጋር ማድረግ ዋነኛ የግብፅ ስትራቴጂ ሆኖ ብቅ አለ፡፡ በ1868 ዓ.ም ግብፃውያን የሸዋ ዋነኛ የንግድ መውጫ የነበረችውን ሀረርን በመቆጣጠር በንጉሥ ምኒልክ ላይ ጫና ለማሳደር ሞከሩ፡፡
የዚህ ስትራቴጂ ዋነኛ ዓላማም ንጉሥ ምኒልክ ከአፄ ዮሐንስ ጋር በነበራቸው አለመግባባት ተጠቅመው የጦር መሣሪያ በማቅረብ ኢትዮጵያ በውስጥ ጦርነት እንድትታመስ ማድረግ ነበር፡፡ ይህ አካሄድ ግብፅ ኢትዮጵያን ከቻለች ለማዳከም፣ ካልቻለች ደግሞ ከፋፍላ ለመጣል እንዴት ስትሠራ እንደኖረች የሚያሳይ የታሪክ ምስክር ነው፡፡
የጉንደት እና የጉራ አንጸባራቂ ድሎች
ነገር ግን አፄ ዮሐንስ የግብፅን የመስፋፋት ዝም ብለው አልተመለከቱትም፡፡ ንጉሡ ትልቅ እንቅፋት በመሆናቸው የተበሳጨችው ግብፅ ከዚያ ቀደም በአሜሪካ የእርስ በርስ ጦርነት እና በ1850ዎቹ የጀርመን ጦርነቶች ልምድ ባካበቱ የዴንማርክ፣ የጀርመን እና የኦስትሪያ የጦር አበጋዞች የሚመራ 15 ሺህ የሚደርስ ግዙፍ ጦር አደራጅታ በ1868 ዓ.ም በኢትዮጵያ ላይ አዘመተች፡፡
ሆኖም የግብፅ የሤራ ድር እንደ ሸረሪት ድር በቀላሉ ተበጣጠሰ፡፡ የምፅዋው አስተዳዳሪ ቨርነር ሙንዚንገር ወታደሮቹን ይዞ ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ሲሞክር ኅዳር 7 ቀን 1868 ዓ.ም በአፋር ተዋጊዎች ተከብቦ ከነወታደሮቹ ተደመሰሰ፡፡
ልክ በዚሁ ዕለት አፄ ዮሐንስ ከሰሜን የመጣውን የግብፅ ጦር ጉንደት ላይ ድባቅ መቱት፡፡ ከጥቂት ወራት በኋላ ደግሞ በጀግናው ራስ ዓሉላ አባነጋ መሪነት ጉራ ላይ በተደረገው ጦርነት የግብፅ ጦር ከግማሽ በላይ ኃይሉን በማጣት አሳፋሪ ሽንፈትን ተከናነበ፡፡
ይህ የጉራ ታሪካዊ ሽንፈት የኬዲቭ እስማኤልን የአፍሪካ ግዛትን የማስፋፋት ሕልም ያጨለመ እና ከሥልጣን ለመውረዱ ዋነኛ ምክንያት የሆነ ክስተት ነበር፡፡ ይህ ደማቅ ድል የራስ ዓሉላን ዝና በአህጉሪቱ ከፍ ያደረገ እና የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት ያስመሰከረ ነበር፡፡
የጉራ እና የጉንደት አጥንቶች ዛሬም ቢሆን የሚነግሩን ሕያው እውነት አለ፡፡ ይኸውም አንድነቷን የጠበቀች ኢትዮጵያ የትኛውንም የውጭ ወራሪም ሆነ የውስጥ ሤራ ማክሸፍ እንደምትችል ነው፡፡
ዛሬም ቢሆን የግብፅ የትርምስ ፖሊሲ በተለያየ ገፅታ እየተተገበረ ይገኛል፡፡ ያረጀውን ሤራ ለማክሸፍ ልክ እንደ አባቶቻችን ከውስጥ ሹኩቻ ወጥተን፣ አንድነታችንን አጠናክረን ታሪካዊ ጠላቶቻችንን በጋራ እና በብልሃት ልንመክት ይገባል፡፡
ብሔራዊ ጥቅማችን የሆነውን ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እና ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶቻችንን ከጠላት ሤራ በመጠበቅ ሁላችንም ለሀገራችን ዘብ ልንቆም ይገባል!
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: