የሰው ልጅ የታሪክ ጉዞ በቴክኖሎጂ የረቀቀ ዜማ የተቃኘ ነው። ዓለም የዕለት ተዕለት አኗኗሯን ለማቅለል እና ሥልጣኔን ለማፋጠን ተከታታይ የኢንዱስትሪ አብዮቶችን ስታስተናግድ፣ የሀገራችን የኢትዮጵያ የታሪክ ሒደት ግን ፈጽሞ የተለየ እና በቁጭት የተሞላ መልክ ነበረው።
በ1765 (እ.አ.አ) ዓለም የመጀመሪያውን የኢንዱስትሪ አብዮት አስተናገደች። የድንጋይ ከሰልን ከመሬት ቆፍሮ በማውጣት እና የእንፋሎት ኃይልን በመጠቀም የሜካናይዜሽን ሒደት ተጀመረ።
አህያ እና በቅሎ በባቡር ፉርጎ ሲተኩ፣ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ሲበራከቱ ኢትዮጵያ የት ነበረች? በዚያን ዘመን ሀገራችን በዘመነ መሳፍንት ተከፋፍላ፣ ወደ አንድነት ያልመጣችበት እና እርስ በርስ በመጠፋፋት አዙሪት ውስጥ ትዋለል ነበር።
ምንም እንኳን አኩሪ ጥንታዊ ሥልጣኔዎች ቢኖሩንም፣ ተባብሮ በሀገር ግንባታ እና በቴክኖሎጂ ኃይል ላይ ለማተኮር ገና ሐሳቡ ያልነበረበት ዘመን ነበር። የዓለም የመጀመሪያው የሜካናይዜሽን ባቡር በሩቁ አምለጠን።
በ1870ዎቹ (እ.አ.አ) አካባቢ ሁለተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ፈነዳ። ኤሌክትሪክ፣ ጋዝ እና ዘይት አዳዲስ የኃይል ምንጮች ሆኑ።
በዚህ ዘመን ግን በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ተስፋ ሰጪ የቴክኖሎጂ መነቃቃት ምልክቶች ታይተው ነበር። አፄ ቴዎድሮስ በጋፋት የጀመሩት ጥረት፣ እንዲሁም በ19ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ በአፄ ምኒልክ ዘመን የተጀመሩት የባቡር፣ የስልክ፣ የመኪና፣ የፖስታ እና የኤሌክትሪክ መብራት አገልግሎቶች ሀገራችንን ከዓለም ጋር ለመገናኘት ያደረገቻቸው ታላላቅ እርምጃዎች ነበሩ።
ያኔ የታየው የቴክኖሎጂ ጅማሮ ሳይሰናከል ቢቀጥል ኖሮ፣ ዛሬ ኢትዮጵያ በዓለም የኢንዱስትሪ መድረክ የት በደረሰች ነበር? የሚለው የታሪክ ጥያቄ ሁሌም ቁጭት ይፈጥራል።
ነገር ግን ብሩህ ጅማሮዎቻችን ቀጣይነት አልነበራቸውም። በ1969 (እ.አ.አ) ሦስተኛው አብዮት የኒውክሌር ኃይልን፣ ኤሌክትሮኒክስን እና የኮምፒውተር ቴክኖሎጂን ይዞ ብቅ አለ።
አሜሪካ እና አውሮፓ በኦቶሜሽን ወደ አዲስ ምዕራፍ ሲገሰግሱ፣ ኢትዮጵያ ፍጹም ዘውዳዊ በነበረ ሥርዓት ውስጥ ሆና፣ ሥርዓቱም አቅም እያጣ የመጣበት ጊዜ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ሀገራችን ጭልጥ ወዳለ አብዮት እና መፈራረስ ውስጥ ገባች። ያንን ተከትሎ የሰፋው የፖለቲካ ክፍፍል፣ መቋጫ የሌለው የእርስ በርስ ጦርነት እና በተካረረ የነጠላ ትርክት ግንባታ ሳቢያ ኢትዮጵያ ፊቷን ወደ ልማት እና ቴክኖሎጂ ማዞር አልቻለችም። የፖለቲካ ስብራቱ የተጀመሩትን የኢንዱስትሪ ግንባታ ጭላንጭሎች መልሶ አዳከማቸው። ዓለም ወደ ዲጂታል ዘመን ስትበር እኛ ዳግም ወደ ኋላ ቀረን።
ሆኖም፣ ታሪክ በቁጭት ብቻ አላበቃም። ዛሬ ዓለም በአራተኛው (እና አንዳንዶች አምስተኛው በሚሉት) የኢንዱስትሪ አብዮት ላይ ትገኛለች። የኢንተርኔት፣ የታዳሽ ኃይል፣ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI)፣ የክላውድ ቴክኖሎጂ እና የቨርቹዋል ሪያሊቲ ዘመን!
ከ2018 የአውሮፓውያን አቆጣጠር ሀገራዊ ለውጥ በኋላ ኢትዮጵያ ዳግም በአዲስ መልክ ከእንቅልፏ ነቃች። አሁን የኢትዮጵያ ውሳኔ ግልጽ ነው፡- ያመለጡንን ሦስት አብዮቶች አንድ በአንድ ለመድረስ ማዝገም ሳይሆን፣ ዘመኑን በአቋራጭ ቀድሞ መዝለል (Leapfrogging)!
ይህን ታሪካዊ የዝላይ ዘመን "አንድ እግራችን መሬት ላይ፣ አንድ እግራችን አየር ላይ" በማለት መግለጽ ይቻላል። መሬት ላይ ባለው እግራችን አፈሩን አርሰን የግብርናውን እና የመሠረተ ልማት እውነታችንን እያስተካከልን፣ አየር ላይ ባለው እግራችን ደግሞ የዓለምን የቴክኖሎጂ ጣሪያ የሆነውን የክላውድ ቴክኖሎጂን፣ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን እና ዲጂታል ፈጠራን በልበሙሉነት እንቆጣጠራለን።
ይህ የረጅም ጊዜ ሕልም ሳይሆን የዛሬ ተጨባጭ እውነታችን ነው። በ"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025" ስትራቴጂ በተመዘገበው ስኬት ላይ በመቆም፣ አሁን ደግሞ አድማሱን አስፍቶ ወደ "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ተሸጋግረናል።
አፍሪካን የቀደመው የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት መገንባቱ፣ የላቁ ቴክኖሎጂዎችን የሚያመነጩ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች አቅም መጎልበቱ፣ እንዲሁም አዲስ አበባን እና ሌሎች ቁልፍ ከተሞችን ወደ 'ስማርት ሲቲ' (Smart City) የመቀየር ግዙፍ እርምጃዎች የዚሁ ትንሣኤ ሕያው ማሳያዎች ናቸው። ቴክኖሎጂ ለእኛ የቅንጦት ሳይሆን ከተቆለፍንበት የድህነት አዙሪት መውጫ ድልድያችን ሆኗል።
ኢትዮጵያ ትናንት የከሰል ጭስን፣ የእንፋሎት ባቡርን እና የኮምፒውተርን ዘመን በፖለቲካ መተረማመስ ብታጣም፣ ዛሬ የረቀቀውን የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ አብዮት አታመልጥም።
በዲጂታል ክህሎት የተካነ አዲስ ትውልድ በመፍጠር፣ ከተቆራረጠው የትናንት ታሪክ ቁጭት ተነሥተን ወደ አዲሱ የቴክኖሎጂ ዝላይ ዘመን በሙሉ አቅማችን ገብተናል።
የኢንዱስትሪ አብዮቶች ታሪክ ወደፊት ሲጻፍ፣ የኢትዮጵያ ስም ከዘገየችበት ተነስታ፣ አየር እና መሬትን አጣምራ ዓለምን በዝላይ በተቀላቀለችበት የድል ምዕራፍ በደማቁ ይሰፍራል!
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: