የብልጽግና ፓርቲ የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 በጀት ዓመት መሪ ዕቅድ የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
በመድረኩ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የዋና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህን ጨምሮ የዋና ጽ/ቤት የዘርፍ ኃላፊ ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊዎች እና ሌሎች አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት አቶ አደም ፋራህ እንደገለጹት፣ የ2018 በጀት ዓመት በተቋም ግንባታ፣ በዴሞክራሲ ሥርዓት እና በልማት ሥራዎች ጉልህ ውጤቶች የተመዘገቡበት ዓመት ነው።
በጀት ዓመቱ ከፓርቲ ግንባታ አኳያ ብልጽግና በአደረጃጀት፣ በአሠራር፣ በሰብአዊና ቁሳዊ ሀብት እንዲሁም በማስፈጸም አቅሙ ተጠናክሮ የወጣበት ዓመት መሆኑን የተናገሩት አቶ አደም ፋራህ፣ ድርብርብ ተልእኮዎችን በታቀደው መሠረት ማሳካት የተቻለበት ነው ሲሉ አብራርተዋል።
መላው ሕዝባችን በእያንዳንዱ ተልእኮ ላይ በንቃት በማሳተፍ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ በመደረጉና በባለቤትነት ስሜት ከፓርቲያችን ጎን በመቆሙ፣ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ጉዟችን ጠንካራ መሠረት የጣለውን 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ መንታ ግቦች በላቀ አፈጻጸም ማሳካት ተችሏል ብለዋል።
ልማትና ዴሞክራሲን ጎን ለጎን በማስኬድ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በተሠሩ ዘርፈ ብዙ ተግባራት የላቀ ውጤት መመዝገቡን የገለጹት አቶ አደም ፋራህ፣ የፓርቲውን ግዙፍ አቅም አሟጦ በመጠቀምና የአመራር ሥነ ምግባር ልህቀትን በማረጋገጥ የሕዝባችንን ሁለንተናዊ ብልጽግና እውን ለማድረግ መትጋት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
አክለውም በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን ያብራሩ ሲሆን፣ የአመራርና አባላት ጥራት ማረጋገጥ፣ የብሔራዊነት ገዢ ትርክት ማስረጽና የፓርቲ ተቋማዊ ስታንዳርዳይዜሽን ሥርዓት ግንባታ ላይ በተጠናከረ መንገድ ይሠራል። ለዚህም የፓርቲያችን አመራር፣ አባላትና የመላው ሕዝብ ርብርብ እጅግ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ለሁለት ተከታታይ ቀናት በሚቆየው በዚህ መድረክ በ2018 ዓ.ም አፈጻጸም ሪፖርት እና በ2019 ዓ.ም መሪ ዕቅድ ላይ ጥልቅ ውይይት ይደረጋል፣ ቀጣይ አቅጣጫዎችም ይቀመጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ከፓርቲው ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: