Search

የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ጋሻ፦ የዘመናዊው የመከላከያ ሠራዊታችን አቅም፣ ጀግንነት እና የላቀ መሥዋዕትነት

ማክሰኞ ሐምሌ 14, 2018 93

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሀገር ሉዓላዊነት እና የሕዝብ አንድነት የመጨረሻው ምሽግ፣ መከራ እና ፈተናዎችን ሁሉ በድል የሚሻገር የቁርጥ ቀን ጋሻ ነው።

ይህ ሠራዊት ታሪክን የሚያነብብ ብቻ ሳይሆን በደሙ እና በአጥንቱ ደማቅ ታሪክን የሚጽፍ፣ ከውስጥም ሆነ ከውጭ የሚቃጡ የውክልና ጥቃቶችን እና ታሪካዊ ሴራዎችን በማክሸፍ ኢትዮጵያን በጽኑ ዓለት ላይ ያቆመ ብሔራዊ ተቋም ነው።

ሠራዊታችን ሀገርን ከብተና፣ ሕዝብን ከጥፋት ለመታደግ ሌሊት እና ቀን በየግንባሩ እየከፈለ ያለው ሀገራዊ መሥዋዕትነት ወደር የማይገኝለት እጅግ የላቀ የጀግንነት ማሳያ ነው።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተደረገው መሠረታዊ የሪፎርም ሥራ ሠራዊቱ ከማንኛውም የፖለቲካና የብሔር ወገንተኝነት የጸዳ፣ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ብቻ ማዕከል ያደረገ ፕሮፌሽናልና ኤሊት ኃይል ሆኖ ዳግም ተገንብቷል።

ይህ የትራንስፎርሜሽን ጉዞ የሠራዊቱን አደረጃጀት፣ ስምሪት እና አስተሳሰብ ሙሉ በሙሉ በመቀየር፣ ሀገራችን ቋሚ እና ጠንካራ ተቋማዊ መሠረት ያላት እንድትሆን አድርጓል።

በተለይም ልዩ የዘመቻ ኃይሎች፣ አየር ወለድ፣ ኮማንዶ፣ የሪፐብሊካን ጋርድ እንዲሁም ሌሎች የልዩ ኃይል ክፍሎች በላቀ ሥልጠና እና ቁመና ተደራጅተው፣ እጅግ ውስብስብ የሆኑ ሀገራዊ ግዳጆችን በብቃት እየፈጸሙ መሆናቸው ይታወቃል።

ከዘመኑ ጋር እኩል ለመራመድ የተደረገው የቴክኖሎጂ ሽግግር የሠራዊታችንን አቅም ወደ አዲስ ምዕራፍ አሸጋግሮታል።

የዘመኑ የጦርነት አካሄድ ከባሕላዊው የሰው ኃይል እና የታንከኛ ውጊያ ተሻግሮ በከፍተኛ ቴክኖሎጂ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ፣ ሠራዊታችን ይህንን ተረድቶ ራሱን በድሮኖች፣ በሳይበር ኦፕሬሽን፣ በኤሌክትሮኒክስ ዋርፌር እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት አደራጅቷል ሲሉ የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገልጸዋል።

ይህ የቴክኖሎጂ አቅም የጠላትን ስትራቴጂካዊ ምሽግ እና መሠረተ ልማት ከርቀት ለማሽመድመድ፣ ውጊያዎችንም በአጭር ጊዜ በድል ለማጠናቀቅ ያስችለዋል። የመከላከያ ኮሌጆችም ይህንን ዘመኑን የዋጀ ስትራቴጂካዊ የደኅንነት ትንተና በማካተትስማርትወታደራዊ አመራሮችን እያፈሩ ይገኛሉ።

የሠራዊታችን ሌላው ግዙፍ መገለጫ እጅግ የላቀ ሕዝባዊ ወገንተኝነቱ እና ወታደራዊ ዲሲፕሊኑ ነው። ግዳጅን በሚፈጽምበት ወቅት የሕግ የበላይነትን እና የውጊያ ሕጎችን አጥብቆ የሚከተል ሲሆን፣ የጠላትን ስብስብ እና ጠንካራ ቋጠሮ ኢላማ አድርጎ ሲመታ ንጹሐን እንዳይጎዱ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጋል።

ይህ የላቀ ሥነ ምግባሩና የሞራል ልዕልናው ሠራዊቱን ከማንኛውም ጸረ ሰላም ኃይል የሚለየው እና የሕዝብ እውነተኛ አለኝታ የሚያደርገው ነው።

ጠላቶች የሠራዊቱን ስም ለማጥፋት የሚነዙትን የሐሰት ትርክት በተግባር በማክሸፍ፣ ሠራዊቱ በገባበት አካባቢ ሁሉ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት በማረጋገጥ እውነተኛ ሕዝባዊ ማንነቱን በተደጋጋሚ አስመስክሯል።

በቀጣናው ያለውን ጂኦ-ስትራቴጂካዊ ፉክክር እና ውስብስብ የደኅንነት ሁኔታ ተከትሎ፣ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር እና ታሪካዊ ጸረ ኢትዮጵያ ኃይሎች በውስጥ ተላላኪዎች በኩል የሚሸርቡትን የውክልና ሴራ በማክሸፍ መከላከያ ሠራዊታችን የቆመበት ጽናት አኩሪ ነው።

ያለ ጦርነት መዋል ማደር የማይችሉ ተላላኪ ኃይሎች ሀገርን ለማዳከም ቢሞክሩም፣ በጠንካራ የአርበኝነት ታሪክ ላይ የተገነባው የጀግናው መከላከያ ሠራዊታችን አንድነት እና የላቀ አቅም ጠላቶቻችንን በቅርብም በሩቅም መምታት የሚችልበት ቁመና ላይ ደርሷል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሀገርን በማዳን፣ ሰላምን በማጽናት እና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በማስከበር ረገድ እየሠራው ያለው ታሪክ ሠሪ ገድል በወርቅ ቀለም የሚጻፍ ነው። በቀይ መለዮው ደምቆ፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታጥቆ፣ በብሔራዊ ፍቅር ታንጾ የኢትዮጵያን ከፍታና ብልጽግና ለማረጋገጥ የሚተጋው ይህ ሠራዊት፤ የሀገር ኩራት፣ የሰላም ዋስትናና የትውልድ አርአያ ሆኖ ለዘላለም ይኖራል።

በበረከት ሽመልስ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: