ማንቸሰትር ዩናይትድ በአዲሱ የውድድር ዓመት ራሱን ለማጠናከር ወደ ቡድኑ ያመጣቸዋል ተብለው ከሚጠበቁ ተጫዋቾች መሀል ሴኔጋላዊው ኢስማኢላ ሳር አንዱ ነው። ይህ ዝውውር የሚሳካ ከሆነ ከአንድሬ ሳንቶስ እና ዩሪ ቴሌማንስ በኋላ ግዝፈት ያለው ዝውውር ይሆናል። በቡድኑ ውስጥ የሚገኙ አፍሪካውያን ተጫዋቾችን ቁጥርም ከፍ ያደርገዋል።
ይህን ዝውውር ለመሳካት ሩቅ አያደርጉትም ከተባሉት ጉዳዮች አንዱ ተጫዋቹ ስለ ላንክ ሻየሩ ክለብ ሰንዝሮታል የተባለው አስተያየት ነው። የእንግሊዙን ድረ ገፅ ቲም ቶክን በመጥቀስ የተለያዩ መገናኛ ንዙሃን እያስተጋቡት ያለው ሀሳብ፤ የ28 ዓመቱ ተጫዋች ወደ ኦልድ ትራፎርድ የማምራት ፅኑ ፍላጎት እንዳለው ነው።
የክሪስታል ፓላሱ አጥቂ የወደፊት ህልሙ የት ክለብ መጫወት እንደሆነ ለቀረበለት ጥያቄ መልሱ ማንቸስተር ዩናይትድ ሆኗል። “እውነት ለመናገር ከልጅነቴ ጀምሮ ስደግፈው ያደግኩት አንድ ክለብ አለ፤ ማንቸስተር ዩናይትድን ከልቤ እወደዋለሁ፤ ከልብ ደጋፊዎቹም አንዱ ነኝ።” ይህ ሃሳብ ነው ተጫዋቹን በቀጣዩ የውድድር ዘመን በቀዩ መለያ ልንመለከተው እንችላለን የሚሉ ግምቶች እንዲበረክቱ ያደረገው።
ተጫዋቹ ስለ ማንቸስተር ዩናይትድ ድጋፍ እና ፍቅሩ ባነሳበት ቃለ-መጠይቅ ከክሪስታል ፓላስ ጋር ተጨማሪ የ3 ዓመት ውል የሚቀረው መሆኑን ተከትሎ፤ ይህ ፍላጎቱ በፓላስ ተጫዋቹን የማዘዋወር ፍላጎት ላይ እንደሚመሰረት ገልጿል።
ኢስማኢላ ሳር በቀደመው የውድድር ዘመን ክሪስታል ፓላስ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የአውሮፓ ኮንፈረንስ ሊግ ዋንጫን ሲያነሳ 9 ግቦችን በማስቆጠር የውድድሩ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ በመሆን ለሻምፒዮንነቱ ጉልህ አስተዋፅኦ አበርክቷል። ከኮንፈረንስ ሊግ ዋንጫ በተጨማሪ፤ በ2024-25 የውድድር ዘመን የኤፍ ኤ እና የኮሚኒቲ ሺልድ ዋንጫዎችን አንስቷል።
በተጠናቀቀው የዓለም ዋንጫ ሴኔጋል ጉዞዋ በ32ቱ ሀገራት ጥሎ ማለፍ በቤልጂየም ተሸንፋ ቢገታም፤ ኢስማኢላ ሳር በአራቱም ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ፣ አራት ግቦች በማስቆጠር አንድ ለግብ የሚሆን ኳስ አመቻችቶ አቀብሏል።
በሴኔጋል ሴንት ሉዊስ ከተማ የተወለደው ኢስማኢላ ሳር እግር ኳስን በሀገሩ በሚገኘው ጄነሬሽን ፉት ክለብ ነው የጀመረው። እንደ በርካታ ሴኔጋላውያን ተጫዋቾች እርሱም የፕሮፌሽናል የክለብ ተጫዋችነት መንገዱን የጀመረው ፈረንሳይ ውስጥ ሲሆን፤ የሊግ አንድ ክለቡ ሜትዝ ቀዳሚው ክለብ ነው።
ሬንስ፣ ዋትፎርድ፣ ኦሊምፒክ ደ ማርሴይ እና ክሪስታል ፓላስ ተጫውቶ ያሳለፈባቸው ክለቦች ናቸው። ለሴኔጋል ዋናው ብሔራዊ ቡድን ደግሞ ላለፉት 10 ዓመታት የተጫወተ ሲሆን፤ በ2019 የአፍሪካ ዋንጫን ያነሳበትን ጨምሮ በ88 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ 23 ግቦችን ከመረብ አሳርፏል።
ኢስማኢላ ሳር በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በሁሉም ውድድሮች ያስቆጠራቸው 20 ግቦችና የሚገኝበት ወቅታዊ አቋም፣ ዩናይትድን የቤንጃሚን ሼሽኮ አማራጭ ሊያደርገው እንዲያስብ ያደረገ ጉዳይ ነው። “ብቸኛው የህልሜ ክለብ” ላለው ማንቸስተር ዩናይትድ ፊርማውን ያኖራል ወይ? የሚለው በጉጉት የሚጠበቅ ጉዳይ ሆኗል።
ክሪስታል ፓላስ ለኢስማኢላ ሳር ዝውውር 50 ሚሊዮን ፓውንድ ሂሳብ ያስቀመጠ ሲሆን፤ በዝውውር መስኮቱ ንቁ ተሳትፎ እያደረገ የሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድ ጆሹዋ ዚርክዚን የድርድሩ አካል ሊያደርገው እንደሚፈልግ መረጃዎች ያመለክታሉ።
በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት አጋማሽ በማይክል ካሪክ አሰልጣኝነት መመራት የጀመረው ማንቸስተር ዩናይትድ ከነበረበት ውጤት አልባ መንገድ ወጥቶ፣ 3ኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ ወደ አውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ መመለሱ ይታወቃል። በሊጉም ከሻምፒዮኑ አርሰናል በተጨማሪ በአዳዲስ አሰልጣኞች ከመጡት ማንቸስተር ሲቲ፣ ቼልሲ እና ሊቨርፑልን ከመሰሉ ቡድኖች ብርቱ ፉክክር ይጠብቀዋል።
በእድሪስ አህመድ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: