የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ስኬት ከሀገራዊ የፖለቲካ መረጋጋት ባሻገር ለሀገራችን ሁለንተናዊ ብልፅግና ጠንካራ መሰረት የሚጥል ወሳኝ ምሶሶ ነው።
ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ዕድገት ሊመጣ የሚችለው አስተማማኝ ሰላም እና የተረጋጋ የፖለቲካ ምህዳር ሲኖር ብቻ እንደመሆኑ መጠን፣ ይህ ሀገራዊ የምክክር መድረክ ለኢኮኖሚው መነቃቃት ዋና ቁልፍ ሆኖ ያገለግላል።
በተለይም ረጅም ጊዜ የዘለቁ ግጭቶች እና የትርክት ልዩነቶች በሀገራዊ ምክክሩ አማካኝነት በሰላማዊ መንገድ እልባት ሲያገኙ ትልቅ ሀገራዊ ፋይዳ ይኖረዋል። አጨቃጫቂ ጉዳዮች የጋራ መፍትሔ አግኝተው እንደ ማኅበረሰብ መተማመን እና መረጋጋት ይሰፍናል።
በዚህም ሀገራችን ለግጭት እና ለፀጥታ ማስከበር የምታወጣውን ከፍተኛ የሰው እና የገንዘብ ሀብት ወደ አገልግሎት መስጫ ተቋማት፣ መሠረተ-ልማት ግንባታ፣ እንዲሁም ወደ ትምህርት እና ጤና ዘርፍ እንድታዞር ያስችላታል።
ይህ ሰላማዊ ከባቢ ደግሞ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ኢንቨስትመንትን በከፍተኛ ሁኔታ በመሳብ ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድልን ይፈጥራል፤ ሀገራዊ ምርታማነትንም ያሳድጋል።
በአሁኑ ወቅት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መሪነት እየተደረገ ያለው የምክክር ጉባኤ ይህንን ራዕይ ዕውን ለማድረግ የተጀመሩ ተስፋ ሰጪ እርምጃዎች ናቸው።
በምክክሩ ወቅት የሚነሱ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ፍላጎቶች ታይተው የጋራ መግባባት ላይ ሲደረስ፣ ማኅበራዊ ፍትህ እና ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዲሰፍን ያደርጋል።
ይህ ተግባር ድህነትን ከመቀነስ ባለፈ፣ ጠንካራ የማኅበረሰብ ትስስርን በማጎልበት እኩልነት የሰፈነበትን ማኅበራዊ ብልፅግና ዕውን ያደርጋል።
ከዚህም በተጨማሪ ሀገራዊ ምክክሩ ጠንካራ እና ገለልተኛ ተቋማትን ለመገንባት መንገድ በመክፈት ለመልካም አስተዳደር መስፈን ትልቅ አስተዋፅኦ አለው።
ግልፅነት፣ ተጠያቂነት እና የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ሥርዓት ሲገነባ ሙስና እና የሀብት ብክነት ይቀንሳሉ።
በአጠቃላይ ሀገራዊ ምክክሩ ሰላምን፣ ማኅበራዊ ፍትህን እና ጠንካራ ተቋማዊ አሠራርን በማረጋገጥ፣ ኢትዮጵያን ወደ ተሟላ እና ዘላቂ ሁለንተናዊ ብልፅግና የሚያሸጋግር ታሪካዊ ዕድል ነው።
በሔዋን ጌታቸው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: