በአሁኑ ወቅት ወደ ወሳኝ ምዕራፍ የተሸጋገረው ሀገራዊ ምክክር የነገ ሀገር ተረካቢ ለሆነው ወጣት ትውልድ ችግሮችን በውይይት እና በመደማመጥ ብቻ የመፍታት ባህልን የሚያወርስ ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑን የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎች እና ወጣቶች ገለጹ።
በሀገራዊ ምክክሩ ዙሪያ አስተያየታቸውን የሰጡት የከተማዋ ነዋሪዎች፣ በሰለጠነ መንገድ በመወያየት የማይፈታ ሀገራዊ ችግር እንደሌለ ተናግረዋል።
ወጣቱ ትውልድ የመደማመጥ እና ልዩነቶችን በሰላማዊ ውይይት የመፍታት ባህልን እንዲያዳብር የሀገራዊ ምክክሩ አስተዋጽኦ ጉልህ በመሆኑ፣ የወደፊቷን ኢትዮጵያ የሚረከቡ ወጣቶች የምክክሩን ውጤት እንዲፀና የማድረግ ድርብ ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል።
ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም እና ሁለንተናዊ ዕድገት መፍትሔው መደማመጥ እና ምክክር እንጂ መገፋፋት እንዳልሆነ ያነሱት አስተያየት ሰጪዎቹ፤ የምክክሩ ተሳታፊዎች በቂ ጊዜ ወስደው መነጋገራቸው ችግሮችን ከስር መሠረታቸው በዘላቂነት ለመፍታት ያስችላል ሲሉ ገልጸዋል።
መልከ-ብዙ እና ኅብረ-ብሔራዊ ለሆነችው ኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ወሳኝ በመሆኑ፣ ይህ የተገኘው ታሪካዊ ዕድል ለልማትና ለሰላም አዲስ ምዕራፍ እንደሚከፍት ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ሁሉም ወገን ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የየድርሻውን ማበርከት እንዳለበት የጠየቁት የወላይታ ሶዶ ከተማ ወጣቶች፤ በምክክሩ ማጠቃለያ ኢትዮጵያውያን በጋራ አሸናፊ የሚሆኑባቸው ውሳኔዎች እንደሚጠብቁ እና ለውሳኔዎቹ ተግባራዊነት ለመሥራትም ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
በትዕግስቱ ቡቼ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: