Search

በሠለጠነ ምክክር የምትገነባዋ ኢትዮጵያ

ሓሙስ ሐምሌ 16, 2018 65

ኢትዮጵያ ለዘመናት ወደ ኋላ ሲጎትታት የነበረውን የታሪክ አውሎ ነፋስ በጽናት አልፋ፣ የአብሮነት እና የተስፋ ንጋት ጮራ የምታበስርበት ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች።

ይህ አዲስ ምዕራፍ የሀገራዊ የምክክር ሒደት ሲሆን፣ ጥቂት ልሂቃን በዝግ በር ውስጥ የሚደራደሩበት መድረክ ሳይሆን የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ እውነተኛ ድምፅ የሚሰማበት ሆኖ እየተካሄደ ነው።

ምክክሩ ልዩነቶች በውይይት የሚፈቱበት እና የነገዋ ጽኑ ኢትዮጵያ መሠረት የሚጣልበት ነፃ የሐሳብ አውድማ ነው።

ሆኖም ሒደቱን ለማጨለም ከፍተኛ በጀት መድበው በሐሰት መረጃ የሚሸረቡ የጥፋት ኃይሎች መኖራቸው አልቀረም።

እነዚህ አካላት ዓላማቸው የሕዝብን አዕምሮ መበከል እና አብሮነታችንን ማናጋት ቢሆንም፣ መሬት ላይ ያለው እውነት ግን እነዚህን ሐሰተኛ ፕሮፓጋንዳዎች ከሥራቸው እየነቀለ እያጋለጣቸው ነው።

በምክክሩየፖለቲካ ፓርቲዎች አይሳተፉምየሚል ሐሰተኛ ትርክት በስፋት ሲነዛ ይደመጣል። ይህ ትርክት የጠመንጃ እና የጽንፍ ፖለቲካ ቦታ ሲያጣ የሚፈጠር የፍርኃት ጩኸት እንጂ እውነታው ከዚህ እጅግ የራቀ ነው።

ዛሬ የምክክር አዳራሾቹ በተለያዩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ አባላት እና ተወካዮች ደምቀው የሚታዩ ሲሆን ሐሳብ በሐሳብ የሚሸነፍበት የሠለጠነ እና ነፃ መድረክ ተፈጥሯል።

የሀገራዊ ምክክሩ ሒደት ከቀበሌ መዋቅር ጀምሮ እስከ ፌዴራል ደረጃ ድረስ ማንም ሳይገለል ኢትዮጵያውያን የተወከሉበት ነው።

አርሶ አደሩ እና አርብቶ አደሩ፣ ወጣቶች፣ ሴቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች የልባቸውን ትርታ ያለምንም ገደብ የሚያሰሙበት የጋራ ማዕድ ተዘርግቶ ሒደቱ እየተካሄደ ይገኛል።

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ አጀንዳዎቹን ያሰባሰበው በቀጥታ ከታች ከሕዝቡ በመነሣት ሲሆን፣ የዜጎች የዘመናት ጥያቄዎች የውይይቱ ዋና ማዕከል ሆነው ቀርበዋል።

ውይይቱም በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ግልጽ፣ አካታች እና ሚዛናዊ በሆነ መልኩ እየተካሄደ ይገኛል።

የሐሰት ፕሮፓጋንዳዎች የቱንም ያህል ቢራቀቁ እና የተሳሳተ መረጃን እንደ መርዝ ቢረጩም መሬት ላይ ያለውን እውነት ፈጽሞ ማሸነፍ አይችሉም።

ዛሬ ተመካካሪዎች በአክብሮት እና በፍቅር እየተደማመጡ ታሪካዊ ልዩነቶቻቸውን በሠለጠነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ በመፍታት ላይ ናቸው።

እውነተኛ ሰላም እና አብሮነት የሚረጋገጠው ደግሞ የተሳሳተ መረጃን በእውነት በመመከት እና የጋራ ሀገርን በሠለጠነ ምክክር መገንባት ሲቻል ብቻ ነው።

በብሌን ደምበሎ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: