Search

የከሸፈው የግብፅ የትርምስ ሤራ እና የኢትዮጵያ ፅናት

ሓሙስ ሐምሌ 16, 2018 109

የግብፅ የውኃ ፖለቲካ እና ቀጣናዊ የበላይነት ፍላጎት የዛሬ አዲስ ክስተት አይደለም። 19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ የግብፅ ገዢ የነበረው ኸዲቭ ኢስማኤል ፓሻ ኢትዮጵያን በግልፅ ወርሮ በጉንደት እና በጉራዕ ጦርነቶች አሳፋሪ ሽንፈትን ከተከናነበ በኋላ ካይሮ አዲስ ስትራቴጂ ነደፈች።

አዲሱ ስልት የስዊዘርላንዳዊውን የግብፅ ቅጥረኛ ጄኔራል ቨርነር ሙንዚንገርን "ኢትዮጵያን ሁልጊዜም በትርምስ ውስጥ ማቆየት" የሚል ዶክትሪን መሠረት ያደረገ ነበር።

ቀጥተኛ ወረራ እና ጦርነት እንደማያዋጣ የተረዱት የካይሮ ገዢዎች የኢትዮጵያን የውስጥ ልዩነቶች በመጠቀም የእርስ በርስ ግጭት እንዲስፋፋ እና ሀገራችን ደካማ ሆና እንድትቀጥል የዘመናት የሤራ መረባቸውን መዘርጋት ጀመሩ።

ይህ የሙንዚንገር የትርምስ ስትራቴጂ በዘመናዊቷ ግብፅ መሪዎችም በተጠናከረ መልኩ ተግባራዊ ሆኖ ቀጥሏል። 1959ኙን -ፍትሐዊ የዓባይ ውኃ ክፍፍል ስምምነት ብቸኛ ተጠቃሚ ሆና ለመቀጠል የምትሻው ግብፅ 1960ዎቹ ጀምሮ የኤርትራ ነፃነት ግንባርን (ELF) በካይሮ በማቋቋም፣ የጦር መሣሪያ እና የፖለቲካ ድጋፍ በመስጠት የኢትዮጵያን የውስጥ ሰላም ለማናጋት ሰፊ ሥራ ሠርታለች።

የጋማል አብደል ናስር አስተዳደር የፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች ማሰልጠኛ እና መፈንጫ በመሆን እንዲሁም የኢትዮጵያን አየር ክልል በማወክ ጭምር ሀገራችንን ለማዳከም ያልቆፈረው ጉድጓድ አልነበረም። የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ዚያድ ባሬ 1969 . ኢትዮጵያን ሲወርርም ግብፅ የጦር መሣሪያ በማቅረብ እና ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ በመስጠት ግንባር ቀደም ተዋናይ ነበረች።

ፕሬዝዳንት አንዋር ሳዳት እና ሆስኒ ሙባረክ ደግሞ "በዓባይ ወንዝ ላይ ግድብ ከተገነባ በቦምብ እናፈነዳለን" እስከማለት የደረሰ ይፋዊ ዛቻ እና የማሸበር ፖሊሲን በግልፅ ሲያራምዱ ቆይተዋል።

ካይሮ ይህንን ዓላማዋን በውክልና ጦርነት ለማሳካት በተለያዩ የሀገራችን ታሪካዊ ምዕራፎች ውስጥ የኦሮሞ ነፃነት ግንባርን፣  እንዲሁም የሕወሓት ኃይሎችን በፋይናንስ፣ በሥልጠና እና በስለላ መረጃ ስትደግፍ መቆየቷ የአደባባይ ሚስጥር ነው።

በተለይም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከተበሰረ በኋላ ግንባታውን ለማስተጓጎል በማሰብ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን በማስታጠቅ፣ ንጹሃን ዜጎች እንዲገደሉ እና መሰረተ ልማቶች እንዲወድሙ ከፍተኛ ጥረት አድርጋለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ይህን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፣ የሕዳሴውን ግድብ ግንባታ ለማሰናከል እና አካባቢውን ለማስበጥበጥ እስከ 15 ሺህ የሚደርሱ የሰለጠኑ ታጣቂዎች በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተሰማርተው እንደነበር ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያይዘውም ኢትዮጵያውያን የገጠማቸውን የውጭ እና የውስጥ ፈተናዎች በጽናት በመመከት፣ ታላቁን የሕዳሴ ግድብ በደማቸው እና በአጥንታቸው ማኅተም እውን ማድረጋቸውን አረጋግጠዋል።

በተለያዩ ጊዜያት የግብፅ የስለላ መረብ አባላት እና ወኪሎቻቸው በኢትዮጵያ ውስጥ በቁጥጥር ስር መዋላቸው፣ ግብፅ የውስጥ ባንዳዎችን በመመልመል እና በማስታጠቅ ሀገራችንን ለማፍረስ የምታደርገውን ቀጥተኛ የስለላ እና የሽብር ጣልቃ ገብነት በተጨባጭ የሚያረጋግጥ ህያው ማስረጃ ነው።

ከዚህ በተጨማሪም በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በኩል ኢትዮጵያ ለልማት የሚሆን ብድር እና እርዳታ እንዳታገኝ የምታደርገው ዲፕሎማሲያዊ እገዳ ሌላው የዚሁ የትርምስ ስትራቴጂ አካል ነው።

ይህ የግብፅ መንግሥት የትርምስ ስትራቴጂ የኢትዮጵያን መንግሥት እጅ በመጠምዘዝ ፍላጎቷን በግድ ለመጫን ያስችለኛል ብሎ ቢያስብም አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ግን እውነታው ፍጹም ተቃራኒ ሆኗል።

የውስጥ ጉዳያችን ውስጥ ገብቶ መበጥበጥ እና ታጣቂዎችን መደገፍ የሕዝቡን ብሔራዊ አንድነት እና የቁጭት ስሜት ይበልጥ እንዲያጠናክር አድርጎታል። የውጭ ጠላት ጣልቃ ገብነት ሲታይ ኢትዮጵያውያን የውስጥ የፖለቲካ ልዩነታቸውን ወደ ጎን በመተው በጋራ የመቆም የዳበረ ታሪካዊ ልማድ አላቸው።

ግብፅ በፈጠረችው ከፍተኛ ጫና እና የውክልና ጦርነት ልክ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሳይስተጓጎል በከፍተኛ የሕዝብ ተሳትፎ ተገንብቶ ብርሃን መስጠት መጀመሩ የዚሁ የማይናወጥ ፅናት ህያው ማሳያ ነው።

የግብፅ የዘመናት የውክልና ጦርነት እና የትርምስ ስትራቴጂ ዛሬም ቢሆን የኢትዮጵያን የብልፅግና እና የከፍታ ጉዞ ሊገታው አልቻለም፤ ወደፊትም አይችልም።

ብሔራዊ ደኅንነታችንን ለማረጋገጥ እና የውጭ ጣልቃ ገብነትን በዘላቂነት ለመመከት የውስጥ ልዩነቶቻችንን በውይይት እየፈታን በአንድነት መቆም አማራጭ የሌለው የህልውናችን መሰረት ነው።

ጠላቶቻችን ክፍተቶቻችንን ተጠቅመው ሀገራችንን የጦርነት አውድማ ለማድረግ የሚሸርቡትን ሤራ እኛ ደግሞ ልዩነታችንን አጥብበን፣ ሀገራዊ መግባባትን ፈጥረን እና በልማት ተጋግዘን ልናከሽፈው ይገባል።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የስኬት ፍፃሜ የዚህ ፅናት እና የአንድነታችን ህያው ሀውልት ሆኖ ለትውልድ ይሻገራል።

በለሚ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: