Search

ሕገ-ወጡ የህወሓት ቡድን የትግራይ ሕዝብን እና ተተኪውን ትውልድ ለከፋ ስቃይ እየዳረገ ነው

ሓሙስ ሐምሌ 16, 2018 65

ሕገ-ወጡ የህወሓት ቡድን የትግራይ ሕዝብን እና ተተኪውን ትውልድ ለከፋ አደጋና ጉስቁልና እያዳረገ መሆኑን የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና የቀድሞ የሥራ ኃላፊዎች ገለጹ።

የትግራይ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ትዴፓ) ሊቀ-መንበር አረጋዊ በርሔ (/) እንዳሉት፥ ሕገ-ወጡ የህወሓት ቡድን ከተመሠረተበት ማግሥት ጀምሮ ችግሮችን በጠብ-መንጃ አፈሙዝ ለመፍታት የሚሞክር፣ ግትር አቋም ያለው የወንጀለኞች ስብስብ ነው።

በፕሪቶሪያ የተፈረመው የሰላም ስምምነት በተገቢው መንገድ ተግባራዊ እንዳይሆን እንቅፋት ሲፈጥር የቆየው ሕገ-ወጡ ቡድን በአሁኑ ወቅት፣ ሰላማዊ የፖለቲካ አማራጮችን በመዝጋትና ከሻዕቢያ ጋር ያልተቀደሰ ጥምረት በመፍጠር የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር በመፈንቅለ መንግሥት ማፍረሱንም አክለዋል።

በተጨማሪም ወጣቶችንና ሕፃናትን ከቤተሰቦቻቸው ነጥቆ ወደ ጦር ካምፕ በማስገባት ለተለያዩ አካላት የገቢ ምንጭ እያደረጋቸው ይገኛል ብለዋል።

የፌዴራል መንግሥት ለሕገ-ወጡ ቡድን የሚያቀርበው ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪና የሚያሳየው ትዕግሥትም የሕዝቡን ጉስቁልና ለማስቀረት ያለመ መሆኑን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የቀድሞው የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እና የዓረና ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ገብሩ አስራት፥ ሕገ-ወጡ የህወሓት ቡድን ሻዕቢያን ጨምሮ ከተለያዩ ሕገ-ወጥ ኃይሎች ጋር ተጣምሮ የትግራይ ሕዝብን ለከፋ ጉዳት የሚዳርግ የጥፋት ተግባር ላይ በመሰማራት ጠላትነቱን በተጨባጭ ማረጋገጡን ተናግረዋል።

ቡድኑ ለሥልጣን ሲል ከክልሉ ሕዝብ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በመተባበር ለሌላ ግጭት እየተዘጋጀ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ከተባባሪዎቹ አንዱ የሆነው ሻዕቢያ የትግራይ ሕዝብን ለማጥፋት የሚሠራ ስለመሆኑ ቀደም ሲል በክልሉ የፈጸመው ጭፍጨፋና ያስከተለው ውድመት ማረጋገጫ ነው ብለዋል።

የቀድሞዋ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤና የስምረት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የምክር ቤት አባል ኬርያ ኢብራሂም፥ ሕገ-ወጡ የህወሓት ቡድን የትግራይ ተተኪ ትውልድን በመዋቅራዊ አሠራር ሆን ብሎ እያጠፋና እያመከነ መሆኑን ገልጸዋል።

የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት የጥይት ድምፅ በማጥፋት ለክልሉ ሕዝብ ተስፋ የሰጠ ሁነኛ የሰላም በር ቢሆንም፣ ቡድኑ ስምምነቱን ለዳግም ጦርነት ጊዜ መግዣነት በመጠቀም የትግራይ እናቶችን እያስለቀሰ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የቀድሞው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረሕይወት በበኩላቸው፥ ሕገ-ወጡ የህወሓት ቡድን የሰላም ስምነቱን በማፍረስ በትግራይ ክልል የሰብዓዊ መብት ረገጣውን እያጠናከረ መምጣቱን ገልጸዋል።

ቡድኑ ወጣቶችን ለውክልና ጦርነት እየተጠቀመባቸው እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ሕዝብን አሸብሮና አስገድዶ ወታደር የማድረግ ይህ እኩይ ተግባር ከሻዕቢያ የተኮረጀና በአሁኑ ወቅት በስፋት እየተተገበረ ያለ አደገኛ ድርጊት መሆኑን አስረድተዋል።

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: