በሃይማኖት እኩልነት እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በኅብረተሰቡ ውስጥ የተለያዩ መስተጋብሮች ይፈጠራሉ።
በእነዚህ መስተጋብሮች ውስጥ አልፎ አልፎ አሉታዊ የሚባሉ ነገሮች ቢከሰቱም፣ በዋናነት ግን በሃይማኖቶች መካከል ያለው መፈቃቀር፣ መከባበር፣ መረዳዳት፣ መገናኘት እና የጋራ ኅብረት ለሀገር ሰላም እና ዕድገት ያለው ጠቀሜታ እጅግ የጎላ መሆኑን በሀገራዊ ምክክር መድረኩ ላይ የተሳተፉት ሊቀ ብርሃን ቀለምወርቅ ቢምረው ገለጹ።
ሊቀ ብርሃን ቀለምወርቅ፣ በተለይም አሁን በሀገራችን እየተካሄደ ስላለው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ፋይዳ ሲያስረዱ፣ ሒደቱ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ትልቅ ድልድይ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህ የምክክር ጉባኤ ተንጠልጥለው ያሉ ጉዳዮች እልባት እንዲያገኙ የሚያደርግ፣ የተበተኑትን የሚሰበስብ እና ያልተቋጩ ሀገራዊ ጉዳዮችን በመልካም ደረጃ እንዲቋጩ የሚያስችል ታሪካዊ መድረክ ነው ሲሉም አብራርተዋል።
የሃይማኖት ተቋማት ሚና በሀገር ግንባታ ላይ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው በመጠቆም፣ ሃይማኖቶች እና የሃይማኖት አባቶች እርስ በርሳቸው ሲፈቃቀሩ እና ሲከባበሩ ለሀገር እጅግ እንደሚበጁ ገልጸዋል።
ሕዝቡንም በመልካም ሥነ ምግባር አንጸው ሲመክሩ እና ለሀገር የሚጠቅም በጎ ተግባር እንዲሠራ ሲያደርጉ የሀገር ሰላም እና አንድነት ይበልጥ ይጠነክራል ነው ያሉት።
ሊቀ ብርሃን ቀለምወርቅ ቢምረው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤውን የወደፊት ስኬት በተመለከተ ያላቸውን ብሩህ ተስፋ አጋርተዋል።
የዚህ ሀገር አቀፍ የምክክር ጉባኤ ውጤት እና ስኬት፣ ወደፊት የታሰበውን ሀገራዊ ራዕይ በሙሉ እውን የሚያደርግ እና ግቡን የሚመታ መሆኑን አምናለሁ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በሔዋን ጌታቸው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: