Search

ወታደራዊ አካዳሚዎችን ወደ ቀድሞ ክብራቸው የመለሰው የመከላከያ ሪፎርም

ሓሙስ ሐምሌ 16, 2018 79

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ወታደራዊ ታሪክ ጠንካራ መሠረት የተጣለው እንደ ሆለታ ገነት እና የሐረር ጦር አካዳሚ በመሳሰሉ አንጋፋ ተቋማት ነው።

እነዚህ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከታላላቅ የጦር ትምህርት ቤቶች ጋር ተወዳዳሪ የነበሩ አካዳሚዎች፣ ሀገራዊ ሉዓላዊነትን ከማስከበር ባለፈ በኮሪያ እና ኮንጎ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች የኢትዮጵያን ስም ከፍ ያደረጉ፣ ምሁራንና ስትራቴጂካዊ የጦር መሪዎችን ያፈሩ የልህቀት ማዕከላት ነበሩ።

ይሁን እንጂ ተከታታይ የፖለቲካ ሥርዓቶች በወሰዷቸው የተሳሳቱ ውሳኔዎች በተለይም በደርግ ዘመን የተፈጸመውን የከፍተኛ መኮንኖች ግድያ እና አካዳሚዎችን የመዝጋት እርምጃ፣ እንዲሁም 1983 . በኋላ መከላከያን ከሙያዊ ብቃት ይልቅ የፓርቲ ታማኝነት ማዕከል በማድረግ በተሠራው ስህተት እነዚህ ታሪካዊ ተቋማት ገጽታቸውን እና ጥራታቸውን አጥተው በታሪክ ማኅደር ብቻ እንዲቀሩ ተገድደው ነበር።

ይህንን የታሪክ ስህተት በማረም የጦር አካዳሚዎቻችንን ዳግም ትንሣኤ እውን ያደረገው ባለፉት ስምንት ዓመታት የተካሄደው እና አሁንም የቀጠለው ሁለገብ የመከላከያ ሪፎርም ነው።

የሪፎርሙ ትልቁ ስኬት ሠራዊቱ ከፓርቲ ታዛዥነት ሙሉ በሙሉ ወጥቶ ለሕገ-መንግሥቱ እና ለሀገር ሉዓላዊነት ብቻ የሚቆም እውነተኛ ብሔራዊ ተቋም እንዲሆን መደረጉ ነው።

የሰው ኃይል ልማትን ማዕከል ያደረገው ይህ የለውጥ ጉዞ ለረጅም ዓመታት ተዘግተው የነበሩትን ታሪካዊ የጦር አካዳሚዎች በዘመናዊ መልክ በማደራጀት ዳግም ወደ ሥልጠና አስገብቷል።

በዚህም ተቋማቱ የቀድሞ ክብራቸውን ተላብሰው ለዘመኑ የሚመጥን ወታደራዊ ዕውቀት ማፍለቅ ጀምረዋል።

ከአካዳሚዎቹ መከፈት ባሻገር በመከላከያ ዩኒቨርሲቲ በኩል የተደረገው የካሪኩለም ክለሳ የሪፎርሙን ጥልቀት በግልጽ ያሳያል። ሠራዊቱ የዘመኑን ቴክኖሎጂ የዋጀ አቅም እንዲገነባ፣ በሳይበር ደኅንነት፣ በባሕር ኃይል ኢንጂነሪንግ፣ በቴክኖሎጂ ፈጠራ እና በስትራቴጂካዊ አመራር የተካኑ ዘመናዊ መኮንኖች በስፋት እየተፈሩ ይገኛሉ።

ይህ የሰው ኃይል ብቃት ላይ ትኩረት ተደርጎ የተሠራው ሥራ የተቋሙን የፈጠራ አቅም በከፍተኛ ደረጃ አሳድጎታል። በዋናነትም ከዚህ ቀደም ከጥቅም ውጪ ሆነው ተጥለው የነበሩ ከባድ መሣሪያዎች እና ሚሳኤሎች በሀገር ውስጥ አቅም ዳግም እየታደሱ እና የሠራዊቱን የውጊያ አቅም እያጎለበቱ መሆናቸው የዚህ ሪፎርም አንጸባራቂ ፍሬ ነው።

ይህ የተቋማት መታደስ እና የሰው ኃይል የቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሀገራዊ ሉዓላዊነትን ከማስከበር አልፎ የቀጣናውን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሚችል የማይበገር ዘመናዊ ኃይል እንዲሆን ጽኑ መሠረት ጥሏል።

ሪፎርሙ የትላንት ታሪካዊ ስብራታችንን ጠግኖ የነገዋን ጠንካራ ኢትዮጵያ ወታደራዊ አቅም እና ክብር በተጨባጭ መልሷል።

በለሚ ታደሰ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: