የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በነባሩ የሕግ ማዕቀፍ መሠረት በግልጽ ፈቃድ ካልሰጠ በስተቀር፣ ምናባዊ (ቨርቹዋል) ንብረቶችን (Virtual Assets) መጠቀም፣ መግዛት፣ መሸጥ፣ መለወጥ፣ ማስተላለፍ፣ መገበያየት፣ ማወራረድ እና ግብይቶችን ማመቻቸት በጥብቅ የተከለከለ መሆኑን በድጋሚ አሳሰበ።
ባንኩ እንዳስታወቀው፣ ይህ ክልከላ በክሪፕቶ ከረንሲዎች (Cryptocurrencies) ላይ ብቻ የተገደበ ሳይሆን፣ በኤሌክትሮኒክ መንገድ ሊገበያዩ፣ ሊተላለፉ፣ ሊለወጡ እንዲሁም ለክፍያ፣ ለኢንቨስትመንት አሊያም ለተመሳሳይ ዓላማዎች ሊውሉ የሚችሉ ዲጂታል የዋጋ መግለጫዎችን በሙሉ የሚያጠቃልል ነው።
በመግለጫው መሠረት ክልከላው የሚተገበርባቸው ዋና ዋና ተግባራት የሚከተሉትን ያካትታሉ፡-
• በቨርቹዋል ንብረቶች እና በመደበኛ (ሕጋዊ) ገንዘቦች (Fiat currencies) መካከል የሚደረግ ልውውጥ፤
• በአንድ ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ የቨርቹዋል ንብረት ዓይነቶች መካከል የሚደረግ ልውውጥ፤
• የቨርቹዋል ንብረቶች ዝውውር፤
• ቨርቹዋል ንብረቶችን ወይም እነሱን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ መሳሪያዎችን በደህንነት ማስቀመጥ እና/ወይም ማስተዳደር፤ እንዲሁም
• ቨርቹዋል ንብረትን ከማቅረብ እና/ወይም ከመሸጥ ጋር በተያያዙ የፋይናንስ አገልግሎቶች ላይ መሳተፍ እና አገልግሎቱን መስጠት።
በመሆኑም ኅብረተሰቡ ከላይ በተገለጹት ማናቸውም የቨርቹዋል ንብረት ግብይቶች እና ተግባራት ላይ ከመሳተፍ እንዲቆጠብ እንዲሁም ከሕግ ተጠያቂነት፣ ከመጭበርበር፣ ከመታለል፣ ከሳይበር ደኅንነት ስጋቶች፣ ከአሠራር ውድቀቶች፣ ከገበያ መዛባት እና ከከፍተኛ የፋይናንስ ኪሳራ አደጋዎች ራሱን እንዲጠብቅ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጥብቅ ማሳሰቢያ አስተላልፏል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: