የሰው ልጅ የታሪክ ጉዞ በውጣ ውረዶች፣ የርስበርስ ግጭቶችና መለያየቶች የታጀበ ቢሆንም፣ የዘመናችን ኢትዮጵያዊ ትውልድ ግን በሀገሩ ምድር አዲስና ብሩህ የታሪክ ምዕራፍ እየፃፈ ይገኛል።
አዲሱ ትውልድ ከግጭት ይልቅ ሰላምን፣ ከጦርነት ይልቅ የጠረጴዛ ዙሪያ መመካከርን፣ እንዲሁም ከውድመት ይልቅ የተፋጠነ ልማትን በተግባር መርጦ እያረጋገጠ ነው።
ለዘመናት የልዩነትና የግጭት አዙሪት ውስጥ ስትፈተን የነበረችው ሀገራችን ኢትዮጵያ፣ ዛሬ ላይ የሰላምና የለውጥ አርበኛ በሆነው ዜጋዋ ትከሻ ከፍ ብላ ወደ ሁለንተናዊ ብልፅግና ማማ እየተሸጋገረች ትገኛለች። ይህ ሂደት የትውልድ ስብራት የሚጠገንበት፣ ወንድማማችነት የሚጎለብትበትና አወንታዊ ሰላም በፅኑ መሰረት ላይ የሚገነባበት ታሪካዊ ሽግግር ነው።
የመመካከር ባህልና የሰላም ኃይል መሆን
ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ፣ በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ፣ በሚያስገርም ሁኔታ ኢትዮጵያ ሰላምን ብቻ የምትፈልግና ለሰላም ዘብ የምትቆም የሰላም ኃይል ሆናለች።
ጦርነትና ግጭት አውዳሚና የኋሊት ጉዞ መሆናቸውን ጠንቅቆ በመገንዘብ፣ መንግሥት የፖለቲካ ልዩነቶችን በሰለጠነ መድረክና በውይይት ለመፍታት የሚያስችሉ ታሪካዊ እርምጃዎችን በድፍረት ወስዷል። ለዚህም ጉልህ ማሳያ የሚሆነው፣ ለዘመናት ሲያገዳድሉ የነበሩ አጀንዳዎች በንግግር የሚፈቱበትን እድል የከፈተው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱ ነው።
በተጨማሪም፣ የሰሜኑን ጦርነት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በመቋጨት፣ የለውጡ አመራር ያለ ደም መፋሰስ፣ ከእልህና ከግትርነት ነፃ በመሆን ለሰላምና ለድርድር ያለውን የማይናወጥ ቁርጠኝነት በተግባር አሳይቷል። ሀገሪቱ ካለፈው የፅንፈኝነትና የጥላቻ ትርክት በመላቀቅ፣ በወንድማማችነትና እህትማማችነት እሴት ላይ የተመሰረተ አሰባሳቢ ትርክትን እየገነባች ነው።
ጠንካራ የፀጥታ ተቋማት ለዘላቂ ሰላም
ሰላምን ዘላቂ ለማድረግ፣ የሕግ የበላይነትን ለማስፈንና የለውጡን ፍሬዎች ለማስጠበቅ፣ ጠንካራ፣ ገለልተኛና ዘመናዊ ተቋማትን መገንባት ወሳኝ መሆኑ ታምኖበታል። በዚህም መሰረት፣ የፌደራልና የክልል የፖሊስና የጸጥታ አካላትን በማጠናከር፣ እንዲሁም የመከላከያ ሠራዊታችንን ይበልጥ በማጎልበት የዜጎችን ደህንነት የማረጋገጥ ስራ በልዩ ትኩረት ተሰርቷል።
ከለውጡ በፊት ለፖለቲካ ወገንተኝነት ያደሩ የነበሩት የጸጥታና ደህንነት ተቋማት፣ ዛሬ ላይ ሕገ-መንግሥቱን ብቻ መሠረት አድርገው ኢትዮጵያን ብቻ እንዲያገለግሉ የሚያስችል ጥልቅ የሕግ፣ የአሠራርና የአደረጃጀት ሪፎርም ተደርጎላቸዋል።
የጸጥታ አካላቱ ዘመናዊ የመከላከያ ቴክኖሎጂዎችን በማላመድና በመፍጠር፣ ሀገርን ከውስጥም ከውጭም አደጋዎች በአስተማማኝ ሁኔታ የሚከላከሉ የሰላማችን ጽኑ ዘብ ሆነዋል። እነዚህ ተቋማት የሕግ የበላይነትን በማስከበር ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን በማጎልበት ረገድ የላቀ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ።
ከውድመት ወደ ፈጣን ልማት ሽግግር
የሰላም እሴት መጎልበት ኢትዮጵያን ወደ ፈጣን የልማት አቅጣጫ እንድትገሰግስ አድርጓታል። ከጦርነት ይልቅ መመካከርን የመረጠው ትውልድ፣ ኢትዮጵያ ፊቷን ወደ ልማትና ብልፅግና እንድታዞር አስችሏል። የሕዳሴ ግድብን ከነበረበት ውስብስብ ችግር አላቆ ለፍፃሜ ማብቃት፣ በስንዴ ልማት ራስን መቻል፣ እንዲሁም በገበታ ለሀገር እና በኮሪደር ልማት ከተሞችንና የቱሪስት መዳረሻዎችን ማዘመን ሰላም ያመጣቸው በረከቶች ናቸው።
ይህ የሰላም አርበኛ ትውልድ በፈጠረው ምቹ መደላድል፣ ሀገራችን ለውጭ ኢንቨስትመንት መዳረሻ በመሆንና የኢኮኖሚ አቅሟን በማጎልበት የሕዝቦቿን የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ በተግባር እየመለሰች ትገኛለች።
በአጠቃላይ፣ ይህ የለውጥ ዘመን የፈጠረው ትውልድ እውነተኛ የሰላምና የለውጥ አርበኛ ነው። ትውልዱ የትናንትናውን የመጠፋፋትና የዜሮ ድምር ፖለቲካ ታሪክ አድርጎ፣ የሐሳብ ልዕልና የበላይ የሚሆንበትን የሰለጠነ የዴሞክራሲ ባህል በተግባር እያጎለበተ ነው። ከግጭት ፊቱን አዙሮ፣ ጉልበቱን ለታላላቅ የልማት፣ የግብርና፣ የኢንዱስትሪና የመሰረተ ልማት ስራዎች በማዋል የኢትዮጵያን ብልፅግና እያረጋገጠ ይገኛል።
ጠንካራና ሀገር አስቀጣይ ተቋማት፣ የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል፣ እና ፅኑ የሰላም ፍላጎት የተዋሃዱባት የዛሬዋ ኢትዮጵያ፣ የነገውን ብሩህ ተስፋ በልጆቿ እጅ ሰንቃለች። ይህ አለመቻልን የረታ የሰላም ትውልድ፣ የሀገራችንን ሉዓላዊነትና ልዕልና ዳግም በማረጋገጥ፣ ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ የአፍሪካ የብልፅግና፣ የትብብርና የሰላም ተምሳሌት አድርጎ ያቆማታል።
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: