Search

ክንዱ የማይታጠፈው የጀግኖች አምባ!

ቅዳሜ ሐምሌ 18, 2018 176

እስቲ ለአፍታ ቆም ብለን እናስብ፤ የዛሬዋ ኢትዮጵያ የጸጥታና የሉዓላዊነት ምሽግ ምን ያህል ጠንካራ ነው? የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ዛሬ የተረከበውን ሀገራዊ አደራ ታሪክን በሚቀይር የልህቀት ከፍታ ላይ አድርሶታል።

እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ በልዩ የሀገር ፍቅር ስሜት እና በጽኑ ኩራት የሚያስደምመው ይህ ተቋም፣ በጥልቅ ሪፎርም ዳግም የተወለደ የሉዓላዊነታችን ሕያው ምሽግ ነው። ሠራዊታችን ዛሬ በተግባር ያረጋገጠው አቅም የውጊያ ክህሎትን ማሳደግ ብቻ አይደለም።

ከዚያም በዘለለ፤ ጦርነትን ቀድሞ የማስቀረት፣ የጥፋት ሥጋትን ገና በእንጭጩ የማምከን እና በማያዳግም የቅድመ መከላከል (Deterrence) ሳይንሳዊ ስትራቴጂ ጠላትን የማንበርከክ እጅግ የላቀ አቅም ነው።

ጠላት ክፉ አስቦት ወደ ኋላ በድንጋጤ እንዲያፈገፍግ የሚያደርገው ይህ ዘመኑን የሚዋጅ ወታደራዊ ጥበብ፣ ኢትዮጵያን የማትደፈር የብረት አጥር አድርጓታል።

በምድር ላይ ከሚታየው አንበሳ መሰል የውጊያ ጀግንነት፣ በአየር ላይ ካለው ንስራዊ የበላይነት፣ እንዲሁም ከሁለት አሥርት ዓመታት በኋላ ዳግም ተቋቁሞ የቀይ ባሕርን ቀጣና በንቃት ከሚቃኘው የባሕር ኃይላችን ልዕልና ጀርባ ያለው ትልቁ ምሥጢር፤ በቴክኖሎጂ የታጀበው ታሪካዊ የተቋም ሪፎርም ነው።

በተለይም ዘመናዊ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን (UAVs) አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን እና ዘመን አመጣሽ የጦር ቴክኖሎጂዎችን በላቀ የሳይበር አቅም በማዋሃድ የገነባው የኤሮስፔስ ልዕልና፣ ሀገራችንን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ቀጣናዊ አስፈሪ ኃይል አድርጓታል።

የዘመኑ ሳይንስ በከፍተኛ ደረጃ ያስታጠቃቸው፣ በሥነ ልቦና የገዘፉት የሠራዊቱ አባላት፣ ኢትዮጵያን በላቀ የውጊያ ጥበብ የሚጠብቁ የብረት ካስማዎች ናቸው።

ይህ ታሪካዊና እጅግ ስኬታማ ሪፎርም "ሀገር አስቀድም፣ ራስ አስቀጣይና ብቃት ያለው ተቋም ፍጠር" በሚል የጠለቀ ፖለቲካዊና ተቋማዊ ፍልስፍና የተመራ ነው። መከላከያችን ዛሬ የጦርነት ጋሻችን ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የልማት አቅም፣ የሰላም ኢንጂን እና የሽግግሩ ዘመን ታማኝ ዋልታ ነው።

ሠራዊቱ የፈጠረው ቴክኖሎጂያዊ እና ሳይንሳዊ ብቃት ለሀገር የልማት ጉዞ፣ ለመሠረተ ልማት ደኅንነት እና ለኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነታችን ጥበቃ ትልቅ ትሩፋት እያበረከተ ይገኛል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የነገዋን፣ በለጽጋና ተከብራ የምትኖረውን ጠንካራ ኢትዮጵያ እውን የሚያደርግ የኩራታችን ምንጭ ነው።

ኢትዮጵያ የቱንም ያህል ውጫዊና ውስጣዊ ፈተና ቢገጥማት፣ ይህ በቴክኖሎጂ የረቀቀ፣ በሳይንስ የላቀ፣ ጦርነትን አስቀድሞ በማምከን ዘላቂ ሰላምን የሚያጸና አሸናፊ ኃይል እስካላት ድረስ፣ የማትበገር የነጻነት አምባ ሆና ለዘላለም ትቀጥላለች! ክብራችን፣ ጋሻችን፣ እና የዘመኑ የቴክኖሎጂ ምሽጋችን ለሆነው ጀግናው ሠራዊታችን ማለቂያ የሌለው ክብር ይገባል!

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: