ባለፉት አምስት ዓመታት የኢትዮጵያ ቱሪዝም ዘርፍ ከውሱን የገቢ ምንጭነት ገጽታው በመውጣት፣ ወደ ዋነኛ የሀገር ግንባታ፣ የሰላም ማስፋፊያ እና የኅብረ ብሔራዊ አንድነት መገንቢያ ማኅበራዊ መሣሪያነት የተሸጋገረበት ታሪካዊ ምዕራፍ ተመዝግቧል።
ይህ ስትራቴጂያዊ ሽግግር በዘፈቀደ የመጣ ሳይሆን ሀገራችን በራሷ አቅም እና ዕውቀት ላይ መሠረት አድርጋ በነደፈችው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ውስጥ ዘርፉን እንደ አንድ ጠንካራ ብሔራዊ ምሰሶ አድርጎ የመቅረጽ ጥልቅ ራዕይ ውጤት ነው።
በመደመር መንግሥት ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት እና ተቋማዊ ቁርጠኝነት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተወዳዳሪነት እና ዲፕሎማሲያዊ ገጽታ በከፍተኛ ደረጃ ከፍ አድርጎታል።
ከተለመደው የቱሪዝም አሠራር ባለፈ የስብሰባ፣ የጉዞ እና የኮንፍረንስ (MICE) ስትራቴጂዎች መቀረጻቸው እና የኢ-ቪዛ ዲጂታል አሠራሮች መዘርጋታቸው ኢትዮጵያ ከዘመናዊው ዓለም አቀፍ አሠራር ጋር እንድትራመድ እና ተደራሽነቷ እንዲሰፋ አድርገዋል።
የዚህ የቱሪዝም ዘርፍ ሪፎርም ሒደት ትልቁ ማረጋገጫ ደግሞ በመሬት ላይ እውነታዎችን በመለወጥ የጋራ ማንነትን እና ወንድማማችነትን እያጠናከሩ ያሉት ታላላቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች ናቸው።
እንደ ገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር፣ ገበታ ለትውልድ እና የአዲስ አበባን ገጽታ እንደ ስሟ ውብና አበባ ያደረጉ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች የተፈጥሮና የታሪክ ሀብታችንን ከዘመናዊ የከተማና የአካባቢ ልማት ጋር በማስተሳሰር የኀብረብሔራዊ አንድነታችን ሕያው መገለጫ ሆነዋል።
እንደ እንጦጦ፣ ወንጪ፣ ሃላላ ኬላ፣ ጎርጎራ፣ ሎጎ ሐይቅ ሪዞርት፣ ቤኑና እና ኮይሻ ያሉ የተፈጥሮ ውበት እና ታሪካዊ እሴት ያላቸው አዳዲስ መዳረሻዎች ተገንብተው ወደ ሥራ መግባታቸው የጎብኚዎችን ቁጥር በእጅጉ ማሳደጉ ስኬት ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ማኅበረሰቦች የሚገናኙበት፣ እርስ በርስ የሚተዋወቁበት እና በጋራ እሴቶቻቸው ላይ በመመካከር የውስጥ ሰላምን የሚያጸኑበት ስትራቴጂያዊ የሰላም መድረክ የፈጠረ ክስተት ነው።
በተጨማሪም ይህ ሒደት የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ከማሳደግ ባሻገር በሆቴል፣ በመጓጓዣ፣ በአስጎብኚነት እና በተያያዥ አገልግሎት ዘርፎች በሚሊዮኖች ለሚቆሩ ዜጎች ሰፊ እና ዘላቂ የሥራ ዕድል በመፍጠር የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጡን ከማፋጠኑም በላይ፣ ዜጎች በማንነታቸው እና በጋራ ታሪካቸው ኮርተው፣ በወንድማማችነት እና በእኅትማማችነት የሚተሣሠሩበት ትልቅ ማኅበራዊ ፕሮጀክት ሆኖ ማገልገል ጀምሯል።
በመንግሥት በዓመት የውጭ ቱሪስት ፍሰትን እስከ 7.3 ሚሊዮን ለማድረስ ከተቀመጠው ታላቅ ዕቅድ ባሻገር፣ የመሠረተ ልማት አውታሮችን ማለትም መንገድ፣ ኤሌክትሪክ፣ ውኃ እና ቴሌኮም የማሻሻል እና አዳዲስ የኢኮ-ቱሪዝም መዳረሻዎችን ከመገንባት ጋር ተያይዞ በከፍተኛ ትጋት እየተሠራበት ይገኛል።
በዚህ ሒደት ውስጥ የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ማጠናከር እና አገልግሎቱን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ማዘመን፣ ዜጎች የራሳቸውን ሀገር በቅርበት እንዲያውቁ እና የዘላቂ ሰላም ባለቤት እንዲሆኑ የሚያደርግ ዋነኛ ሞተር ሆኖ እንደሚቀጥል በተደጋጋሚ ተነሥቷል።
በመሆኑም ቱሪዝም አሁን ላይ ከገቢ ምንጭነቱ ባሻገር ለሀገር ግንባታ፣ ለዘላቂ ሰላም እና የኅብረብሔራዊ አንድነት መገንቢያ መሣሪያ መሆኑ በተግባር የተረጋገጠ ሲሆን በቀጣይም በሚሊዮኖች የሚቆጠር ተጨማሪ የሥራ ዕድል በመፍጠር ለዜጎች የኑሮ ደረጃ መሻሻል እና ለዘላቂ ሀገራዊ አንድነት ዋነኛ ዋስትና ሆኖ ያገለግላል።
በበረከት ሽመልስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: