የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት የብሔራዊ ደኀንነት ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ደኅንነት እና ጥቅም ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ቁልፍ የአቅም ግንባታ ማዕከል በመሆን እያገለገለ እንደሚገኝ ገለጹ።
ቋሚ ኮሚቴው በዩኒቨርሲቲው ተገኝቶ የሥራ እንቅስቃሴዎችን ጎብኝቷል።
በጉብኝቱ ወቅት የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ፈቲህ ማሕዲ (ዶ/ር) እንዳሉት ተቋሙ የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅም እና ደኀንነት ለማረጋገጥ የተጀመረውን ጉዞ ይበልጥ ውጤታማ የሚያደርጉ አመራሮችና ባለሙያዎችን በላቀ ብቃት እያሰለጠነ ይገኛል።
የዩኒቨርሰቲው መሠረተ ልማቶች፣ ሥርዓተ ትምህርት እና አጠቃላይ የትምህርት አሰጣጥ ኢትዮጵያን የሚመጥን ተቋም እንዲገነባ ያደረጉ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ይህም የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የተሰጠውን ሀገራዊ ተልዕኮ በብቃት እንዲወጣ ከፍተኛ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።
የቋሚ ኮሚቴው አባል እና የመከላከያና ደኅንነት ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሳዲቅ ዐደም በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የሀገር ተረካቢ ዜጎች የብሔራዊ ደኅንነት አእና ጥቅምን ምንነት ተገንዝበው ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጉልህ ሚና እያበረከተ መሆኑን አስረድተዋል።
ተቋሙ በጥናት እና ምርምር ዘርፍ እያበረከተ ያለውን አስተዋፅዖ አድንቀው፣ ዘመኑን የዋጁ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም እና ለትምህርት ምቹ የሆኑ መሠረተ ልማቶችን በማሟላት ከፍተኛ ተስፋ የሚጣልበት ተቋም መገንባት መቻሉን አብራርተዋል።
የቋሚ ኮሚቴው አባላት የዩኒቨርሲቲውን አጠቃላይ እንቅስቃሴዎች እና የማስፋፊያ መሠረተ ልማቶችን ከመጎብኘታቸውም ባሻገር ከብሔራዊ መረጃና ደኀንነት አገልግሎት አመራሮች ጋር በመሆን በቅጥር ግቢው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ማካሄዳቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኀንነት አገልግሎት መሥሪያ ቤት ያደረሰን መረጃ ያመለክታል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: