Search

ኢትዮጵያን ለመንካት ማንም እንዳያስብ፤ እንዳይሞክርም!

ረቡዕ ሐምሌ 22, 2018 143

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ዛሬ ላይ የገነባው እጅግ አስፈሪ  ግርማ ሞገስ፣ የሰው ሀገር ለመውረር፣ ድንበር ለመጋፋት ወይም በሌሎች ሉዓላዊ ሀገራት ላይ  ጣልቃ ለመግባት የታለመ አይደለም።

ይልቁንም፣ ይህ አስገራሚ ወታደራዊ እና ተቋማዊ ቁመና ኢትዮጵያ በአስተማማኝ የልማት፣ የብልጽግና እና የሰላም ጎዳና ላይ ያለ ስጋት እንድትጓዝ የሚያስችል፣ የማይደፈር የውስጥ አቅም ግንባታ ታሪካዊ ፍሬ ነው።

የሠራዊቱ ዐቢይ ግብ ጦርነትን፣ ሽብርን እና ማናቸውም ዓይነት ኢትዮጵያ ላይ የሚሰነዘሩ ፍላጎቶችን ገና ከመታሰባቸው በፊት ሁለቴ ቆሞ እንዲያስብ የሚያደርግ ከወዲሁ ማስቀረት (Deterrence) ነው።

የጠላት የጥፋት ሐሳቡን ገና በጽንሱ እንዲያኮላሽ፣ አሻጥሩን በምናቡም እንዳያስበው የሚያደርግ የብረት ካስማ መሆን ነው። በመሆኑም ሠራዊቱ የኢትዮጵያ ክብር፣ የግርማ ሞገስ ምንጭ እና አስተማማኝ የልማት ክንድ ሆኖ በመቆም ሀገራዊ ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ ይገኛል።

ይህ ኃያል ተቋም የዘመናት የጀግንነት ቅብብሎሽ ሕያው እና ድንቅ ማሳያ ነው። የዛሬው ሠራዊታችን የኢትዮጵያን ጥልቅ አቅም እና የሕዝቧን ታሪካዊ ጽናት ጠንቅቆ የሚያውቅ፣ ከትናንት አባቶቹ የነበልባልነት ወኔን፣ የማይበገር ሥነ ልቦናን እና የሀገር ፍቅርን በክብር የወረሰ የቁርጥ ቀን ልጅ ነው።

ለሀገሩ ሉዓላዊነት እና ጽናት ዘብ በመቆም፣ ለባንዲራው ክብር እና ነጻነት በታማኝነት የሚወድቅ፣ ድንበሩን እና ምድሩን ለጠላት አሳልፎ የማይሰጥ፣ በክብሩ ፈጽሞ የማይደራደር እና አጥንቱን ለሀገሩ ፍቅር የሚከሰክስ የዘመናችን ጀግና ነው።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሀገራችን የክብር ዘውድ ሆኖ የቆመው በዚህ ወደር የለሽ እና ታሪካዊ የሞራል ልዕልና ነው።

ይሁን እንጂ፣ የሠራዊታችን የዛሬው አስፈሪ አቅም በታሪካዊ ጀግንነት ብቻ የሚገደብ አይደለም። ከትናንቱ ሥነ ልቦናዊ ከፍታ ባሻገር፣ ዛሬ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታጠቀ፣ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እና የላቀውን የሚሊተሪ ሳይንስ ጥበብን በከፍተኛ ደረጃ ያነገበ ብልህ ኃይል ሆኗል። ዩኒቨርሳል የሆነውን የጦር ስትራቴጂያዊ እሳቤ የተላበሰው ይህ ተቋም፣ በምድር፣ በአየር፣ በባሕር እና በሳይበር አውድማዎች የረቀቀ የውጊያ ብቃትን ተጎናጽፏል።

ይህ ሳይንሳዊ እና ቴክኖሎጂያዊ ልዕልና ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ አሸናፊ እና የማይደፈር ሉዓላዊ ሀገር አድርጓታል።

ከሁሉም በላይ የዚህ ኃይል ታላቅነት የሚመነጨው ከተቋማዊ ንጽሕናው ነው። ሠራዊቱ በጥልቅ ሪፎርም ራሱን አጥርቶ፣ ከፖለቲካ አገልጋይነት፣ ከጠባብ የፓርቲ ታማኝነት እና ከወገንተኝነት ፈጽሞ የተላቀቀ እውነተኛ የሕዝብ እና የሀገር ኃይል ሆኗል።

ሠራዊቱ የቆመው ለኢትዮጵያ ዘላቂ ክብር፣ ለሕገ መንግሥቱ የበላይነት እና ለሕዝቦች ሁለንተናዊ ደኅንነት ብቻ ነው። ይህ የላቀ ተቋማዊ ነጻነት የሠራዊቱን የሞራል፣ የትጥቅ እና የዲሲፕሊን አቅሞች በአንድነት በማስተሳሰር፣ ሀገራችንን በማንኛውም ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ በብቃት እና በአስተማማኝነት እንድትጠበቅ አስችሏል።

የነዚህ ሁሉ እሴቶችየታሪክ፣ የቴክኖሎጂ፣ የሳይንስ እና የዲሲፕሊንድምር ውጤት አንድ ታላቅ ሀገራዊ እውነታን አረጋግጧል፡- ኢትዮጵያን ለመንካት ማንም እንዳያስብ፣ እንዳይሞክርም የሚያደርግ ብርቱ ኃይል መገንባቱን!

ዛሬ ላይ ይህንን የቀጣናው ኃያል የሆነ ሠራዊት አይቶ፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመድፈር የሚቃጣው፣ በሀገራችን ላይ ክፉ የሚያልም ምድራዊ ኃይል የለም፤ የሪፎርሙ ዋናው ግቡም ይኸው ማንም ደፍሮ እንዳይመጣ ማድረግ ነው።

ኢትዮጵያ ዛሬ ተዋግታ ሳይሆን፣ ሳትዋጋ የምታሸብር፣ ጦርነት ገጥማ ሳይሆን ዘመኑን በሚዋጅ ወታደራዊ ዝግጁነቷ የምትከበር ሀገር ሆናለች።

የኢትዮጵያን ድንበር ማንም ነክቶ በቀላሉ እንደማያመልጥ እና ፀጥ ሊባል እንደማይችል፣ ሠራዊቱ ባለው ግዙፍ እና አስፈሪ ዝግጁነት በተግባር አሳውቋል።

በመሆኑም ይህ ሠራዊት፣ የሀገር ጽናት፣ የቀጣናው አስፈሪው ግርማ ሞገስ፣ እና የማትደፈረዋ ኢትዮጵያ የዘላለም የሰላም እና የልማት ምሽግ ነው!

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: