ከዓመታት በፊት የዓባይ ወንዝ ተፋሰስ በከፍተኛ የሥነ ምኅዳር መዛባት እና የሕልውና አደጋ ውስጥ ወድቆ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው።
የደን መመናመን፣ ከፍተኛ የአፈር መሸርሸር እና የአካባቢ መራቆት የወንዙን ዘላቂ ደኅንነት አደጋ ላይ ጥለውት ነበር።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር አማካኝነት ይህንን የተፈጥሮ መዛባት ለመቀልበስ ሰፊ ሥራ ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ፣ የተፋሰሱ ሥነ ምኅዳር ዳግም ሕይወት እያገኘ ይገኛል።
ይሁን እንጂ የዓባይ የታችኛው ተፋሰስ ሀገር የሆነችው ግብፅ ይህንን ተጨባጭ ሳይንሳዊ እውነት ከመቀበል ይልቅ አሁንም ፍሬ አልባ በሆነ የፖለቲካ ሴራ እና የዲፕሎማሲ ጫጫታ ውስጥ ትገኛለች።
የአረንጓዴ ዐሻራ ኢኮኖሚያዊ እና ተፈጥሮአዊ ፋይዳ
ከአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በፊት በየዓመቱ ከ100 ሚሊዮን ቶን በላይ አፈር ከኢትዮጵያ ተራሮች እየታጠበ ወደ ታችኛው ተፋሰስ ይጓዝ ነበር።
ይህ አፈር በሱዳን በሚገኙት የሮሴሬስ እና ሴናር፣ እንዲሁም በግብፅ የአስዋን ግድቦች ላይ ከፍተኛ የደለል ክምችት በመፍጠር የግድቦቹን የውኃ መያዝ አቅም በእጅጉ ይቀንሰው ነበር።
ሱዳን እና ግብፅ ይህንን ደለል ለማጽዳት በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ያወጣሉ።
አሁን ግን ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የተከለቻቸው በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞች የአፈር መሸርሸርን በመግታት የደለል ክምችትን በከፍተኛ መጠን መቀነስ ችለዋል።
ይህም የውኃውን ጥራት ከመጨመሩ ባሻገር፣ ለግብፅ እና ለሱዳን በነጻ የተገኘ ትልቅ የኢኮኖሚ እና የአካባቢ ጥበቃ ዕድል ነው።
የሳይንስ እውነት፦ የበረሃ ትነት የቀነሰው ደጋማው የውኃ ባንክ
ሳይንሳዊ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በግብፅ ሞቃታማ የበረሃ አየር ንብረት ውስጥ በሚገኘው የአስዋን ግድብ ላይ ብቻ በየዓመቱ ከ10 እስከ 14 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ በትነት ይጠፋል።
ግብፃውያን በከፍተኛ ሁኔታ ውኃ የሚያጡት በተፈጥሮ ትነት ምክንያት እንጂ በኢትዮጵያ የልማት ፕሮጀክቶች አይደለም።
በተቃራኒው በኢትዮጵያ ቀዝቃዛ ደጋማ አካባቢዎች የተተከሉት ቢሊዮን ዛፎች የዝናብ ውኃ ወደ ከርሰ ምድር እንዲሰርግ በማድረግ፣ ውኃው ሳይተንን እንዲጠበቅ እና በበጋው ወራት እንኳ የተረጋጋ የውኃ ፍሰት እንዲኖር እያደረጉ ነው። የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የተገነባበት ጉባም የትነት መጠንን በእጅጉ በመቀነስ ለቀጣናው አስተማማኝ የውኃ ባንክ ሆኖ ያገለግላል።
ግብፅ ከፖለቲካ ሴራ ወደ ትብብር ብትመጣ የምታገኛቸው ጥቅሞች
የግብፅ ዋነኛ ስሕተት የውኃ ዋስትናን በዲፕሎማሲያዊ ጫና እና በ1929 እንዲሁም በ1959 በተደረጉ ጊዜ ያለፈባቸው የቅኝ ግዛት ውሎች ማግኘት የሚቻል መምሰሉ ነው። እውነታው ግን ተፈጥሮ የወረቀት ስምምነትን አታውቅም። በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ እና የሕዝብ ቁጥር ዕድገት ምክንያት የግብፅን የውኃ ዋስትና የሚያረጋግጠው ብቸኛው መንገድ የውኃ ምንጮችን በጋራ መጠበቅ ብቻ ነው።
ግብፅ ወደ አረንጓዴ ትብብር ብትመጣ በርካታ ትሩፋቶችን ታገኛለች። የመጀመሪያው በከንቱ የሚባክን በጀትን ወደ ልማት ማዞር ነው። ግብፅ ኢትዮጵያን ለማዳከም እና የጦር መሣሪያ ለመግዛት በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ታወጣለች። ይህን ገንዘብ ከኢትዮጵያ ጋር በአረንጓዴ ልማት እና በተፋሰስ ጥበቃ ላይ ብታፈስሰው የዘለቄታ የውኃ ደኅንነቷን ታረጋግጣለች።
ሌላው ትሩፋት የኃይል እና የውኃ ዋስትና ማግኘት ነው። ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እና የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በርካሽ ዋጋ የኤሌክትሪክ ኃይል ከማስገኘታቸውም በላይ፣ በድርቅ ወቅት አስተማማኝ የውኃ አቅርቦት ዋስትና ይሆናሉ።
ድምር ውጤቱ ደግሞ ሁሉም አሸናፊ የሚሆኑበት ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ዲፕሎማሲ ነው። ከቀጣናዊ ውጥረት ይልቅ ለአየር ንብረት ለውጥ መፍትሔ በሚሆኑ አረንጓዴ ፕሮጀክቶች ላይ ከኢትዮጵያ ጋር መሥራት በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ትልቅ አመኔታ እና ድል ያስገኝላታል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዐቢይ መልዕክት
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ደጋግመው እንዳስገነዘቡት የኢትዮጵያ ዓላማ የዓባይን ውኃ ብቻዋን መጠቀም ሳይሆን በመተባበር ማደግ ነው። ግብፅ የውኃ እጥረት እውነትም የሚያሳስባት ከሆነ፣ መፍትሔው በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ወይም በዓረብ ሊግ በሚደረግ የፖለቲካ ዲስኩር አይገኝም።
መፍትሔው ያለው የውኃው ምንጭ በሆነችው ኢትዮጵያ ተራሮች ላይ ነው። ተፈጥሮን ማከም እና አረንጓዴ ዲፕሎማሲ የሕልውና ጉዳይ እንጂ የፖለቲካ ምርጫ አይደለም። በመሆኑም ግብፅ ይህንን ተጨባጭ ሳይንሳዊ እውነት ተረድታ፣ ኢትዮጵያ ያቀረበችላትን የሰላም እና የልማት ጥሪ መቀበሏ አማራጭ የሌለው ብቸኛ መውጫ መንገዷ ነው።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: